በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በምግብ እደላው፣ ገንዘብ በመደበቁ፣ ከአይሁድ ውጭ ወንጌሉን ያለመናገር፣ አሕዛብ የሆኑትን አማኞች ካልተገረዛችሁ እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች መኖራቸውና ማስቸገራቸው አንሶ፤ አሁን ደግሞ ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ወርደው በሰላም የወንጌልን ሥራ የምትሠራውን ቤተ ክርስቲያን ወደ ሙሴ ሥርዓት ካልተመለሳችሁ እያሉ ማስቸገር ጀመሩ፡፡ በሐዋርያት ሥራ 15፡1-2 ላይ እንዲህ ይላል፣ “አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፡- እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡”

በገላትያ 2፡1-5 ላይ እንደምንመለከተው፣ ጳውሎስ ከ14 ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቶ ለአሕዛብ ስለሚሰብከው ወንጌል እውነተኛነትና እግዚአብሔር በእርሱ እንዴት እየሠራበት እንዳለና አሕዛብም እንዴት ወንጌሉን በደስታ እየተቀበሉት እንዳሉ፣ ማስረጃ አሕዛብ (ግሪካዊ) የሆነውን ቲቶን ሳይገረዝ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ በመውጣት፣ አሕዛብ አማኞች መገረዝና ሕግን መጠበቅ እንደሌለባቸው ዋኖች ለነበሩት ለብቻቸው አሳምኖአቸው እንደ ተመለሰ በሚቀጥሉት ቁጥሮች እንመልከት፡፡ “…በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው›› (ቁ.2)፡፡

ከዚህ በፊት በዚህ በገላትያ ምዕራፍ 2 ውስጥ እንደ ተመለከትነው እነጴጥሮስ ወደ ተገረዙት (አይሁድ)፣ እነጳውሎስ ደግሞ ወዳልተገረዙት (አሕዛብ) ዘንድ መሄድ እንዳለባቸው ግድግዳ አቁመው እንደ ተለያዩ ተመልክተናል፡፡ ምናልባትም በአንጾኪያ ያለውን ችግር የፈጠሩት ዋኖቻቸው የተቀበሉትን እውነትና ሐቅ ለመገልበጥ ይመስላል፡፡ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህን የመሰሉ ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ መሪዎችና አገልጋዮች ያላስተማሩትን ምዕመናን ከተለያዩ ሰዎች፣ ካሴቶችና ሲዲዎች ያዩትንና የሰሙትን ሲለማመዱ እንመለከታለን፤ ተው ብንላቸውም በፍጹም አይተውም፡፡

ለምሳሌ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጋንንትን “በስሜ” አውጡ ብሎ ነው ትእዛዝ የሰጠው፣ ሐዋርያትም ያወጡት በስሙ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን  ግን ዛሬ “በኢየሱስ ስም” ብለን አጋንንትን ማውጣት ሲገባን “ስ…ም” በማለት ልዩ ቅላጼ በመስጠት ወይም “ደ…ም” በማለት ለማስወጣት እንሞክራለን፡፡ አጋንንትም ኢየሱስን አውቀዋለሁ “ስ…ም” የምትሉትን ግን አላውቀውም በማለት በአስቄዋ ልጆች ቀልዶባቸው ልብሳቸውን እንደ ቦጫጨቀባቸውና እንዳቆሰላቸው በእኛም ላይ ዛሬ አልወጣም እያለ ይቀልድብናል (የሐዋ.19፡11-16)፡፡

ከይሁዳ ወርደው ስለ ግርዛት በማስተማር ችግር በፈጠሩ ጊዜ፣ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ነገሩን በትዕግስት ይዛ ነገሩን ለማስተካከል ከሁለቱም ወገኖች ሰዎች ተወክለው ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወዳሉበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲወጡ ተወሰነ፡፡ እነጳውሎስ የመጀመሪያውን የወንጌል ጉዞ ጨርሰው እስኪመጡ ድረስ እነዚህ የሐሰት የግርዘት አስተማሪዎች ወደ ጌታ የመጡትን አማኞች ሁሉ ወደ ኋላ ሊመልሱ ነበር  አሳባቸው፣ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ እነጳውሎስ አገልግሎታቸውን ጨርሰው ስለ ተመለሱና ስለ ደረሱባቸው ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

እነጳውሎስ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም በወጡ ጊዜ ከዓላማቸው ሳይደናቀፉ፣ ጊዜ ሳያባክኑ በፊንቄና በሰማርያ ያሉትን አማኞች እየመከሩ በመሄዳቸው ወንድሞች እጅግ ደስ አላቸው፡፡ ኢየሩሳሌም በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም በታላቅ አክብሮት እንደ ተቀበሏቸው ቃሉ ይነግረናል፡፡ ክርክሩም በተጀመረ ጊዜ ጳውሎስ እግዚአብሔር እንዴት በሕይወቱና በአሕዛብ ሕይወት እየሠራ እንዳለ ሲናገር፣ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑት ደግሞ በተራቸው  ተነስተው ሲያስረዱ እንዲህ አሉ፡- “ከፈሪሰውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነስተው፡- ትገርዟቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ” (15፡5)፡፡ በቤተ ክርስቲያን አንድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ችግሩን ለመፍታት በመጀመሪያ በጌታ ፊት በጸሎት መውደቅ ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠልም፣ በአንድ ላይ ሆኖ በውይይት ለመፍታት ርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ትምህርታችን የኢሩሳሌምና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ችግራቸውን በውይይት እንደ ፈቱ እንመለከታለን፡፡  


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *