ጳውሎስ ዜግነቱን ብቻ ሳይሆን፣ በገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረውን ትምህርቱን ተጠቅሞበታል፡፡ እኔ እንደ ምረዳውና የሐዋርያት ሥራን ሳጠና እንዳገኘሁት፣ በኢየሩሳሌም የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን እስከ አሥር ዓመት ድረስ የመሯት ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ምክንያቱም እሰከ ምዕራፍ 11፡1 ድረስ ሽማግሌዎች የሚል ቃል ተጠቅሶ አናገኝም፡፡ ከምዕራፍ 11፡30 ላይ ስንደርስ ግን በርናባስና ጳውሎስ ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ተልከው የተዋጣውን ገንዘብ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በሄዱ ጊዜ ያስረከቡት ለሽማግሌዎች (ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠቀስ) እንደ ሆነ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሉቃስ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እያለ በተደጋጋሚ መጻፉን እናነብባለን፡፡ ስለዚህ በምዕራፍ 14 ላይም ሽማግሌዎችን በየከተማው እየሾመ ይዞር ስለ ነበር፣ የሽምግልናን አገልግሎት እያስጀመረና እየመሠረተ ከአገር ወደ አገር እንደ ዞረ ስመለከት፣ የሽምግልናን አገልግሎት በኢየሩሳሌምም ቢሆን ጳውሎስ አስጀምሮታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም ጳውሎስ በየከተማው ሲሄድ ሽማግሌዎችን እያስመረጠ ሲዞር ምንም ተቃውሞ ሲደርስበት አንመለከትም፡፡ በተለይም በምዕራፍ 15፡4 ላይ በኢየሩሳሌም በተደረገው ጉባኤ ላይ ለመገኘት ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጡ ጊዜ ሲቀበሏቸው የነበረው አቀባበል፣ ሽማግሌዎችን በመሾም ላይ ስምምነት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሰላምታው ሞቅ ያለና አቀባበላቸው ከበሬታ ያለበት ነበረ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ባገለገለው አገልግሎት፣ የራሱን መንግስት መስርቶ ራሱን ስላልሰበከ፣ ምንም ተቃውሞ ሲደርስበት አንመለከትም፡፡ ብዙ ጊዜ ችግር የሚፈጠረው የሥጋ ነገር ሲጨመርበት ነው፡፡

 ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ዕውቀት የበረታ፣ ከዚህ በፊት እንደገለጥኩት፣ በታዋቂው መምህር በገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረ በመሆኑ፣ የካህናትን አገልግሎት በሽማግሌዎች፣ የሌዋውያንን አገልግሎት በዲያቆናት እንደተካው አስባለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ በምዕራፍ 6 ላይ ያሉትን 7 ሰዎች ዲያቆናት እያልን እንጠራቸዋለን እንጂ በመሠረቱ ለድቁና አገልግሎት የተመረጡ አይደሉም፡፡ የተመረጡት በምግብ በኩል ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ነበር፡፡ በግሪክኛው “ዲያቆኖስ” ማለት ማገልገል ማለት ነው፡፡ በኋላ ላይ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሲመረጡ ያንኑ ቃል “ዲያቆንያ” የሚለውን መጠሪያ ተጠቀሙበት እንጂ፣ ሽማግሌዎች ሳይመረጡ ዲያቆናት ተመርጠው ነበር ማለት የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ዲያቆናት ነበሩ አልነበሩም ብሎ መከራከሩ ምንም ጥቅም የለውም፣ ዋናው ቁም ነገር ቤተ ክርስቲያን በጊዜው የተፈጠረውን ችግር በእነርሱ አማካኝነት መፍታት መቻሏ ነው፡፡    

በአንጾኪያ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን እንደ ተባሉ ሁሉ የሽምግልናንና የድቁናን አገለግሎት ጀምረው ይሆናል ወይም ጳውሎስ ከሐዋርያት ጋር ሆኖ አስጀምሮታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ጌታም ሊጠቀምበት የፈለገው ይህን ዕውቀቱን እንደነበረ መረዳት አያስቸግርም፡፡ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ያለንን ዕውቀት ሊጠቀምበት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊም ይሁን ምድራዊ፣ እኛም ያለንን ዕውቀት ለእርሱ ክብር ማዋል አለብን፡፡

ጳውሎስ ሮማዊነቱንና የተማረ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ልበ ሰፊነቱንም እንደተጠቀመበት ከሉቃስ የጽሑፍ ማስረጃ ማየት እንችላለን፡፡ ጳውሎስ ከአይሁድና ከአሕዛብ፣ ከተማሩና ካልተማሩ፣ ከነጮችና ከጥቁሮች፣ ከድኻና ከሃብታም ጋር ሆኖ ማገልገሉ ልበ ሰፊነቱን ያሳያል፡፡ በተለይም በምዕራፍ 14፡27 ላይ ስንመለከት፣ አሕዛብን እንደ ተቀበለና አሕዛብም እንደ ተቀበሉት እናያለን፡፡

ከብርቱ፣ ከደካማው፣ ሕግ ካለውና ከሌለው ጋር ሌሎችን ለመጥቀም ብሎ ያደርገውና ይተባበር እንደነበር ቀደም ብዬ ገልጫለሁ፡፡ ለመሆኑ ልበ ሰፊነቱን ከየት አገኘው? ጳውሎስ በትውልዱ አይሁዳዊ፣ በዜግነቱ ሮማዊ ሲሆን፣ በባሕሉ ደግሞ ግሪካዊ ነበር፡፡ ይህ ማለት የተወለደው ጠርሴስ በተባለች አገር እንደ ሆነ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በግሪክ ባሕል፣ ዕውቀትና ፍልስፍና በማደጉ ልበ ሰፊ እንዲሆን እንደረዳው ማየት ይቻላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መደገፉና መመራቱ ለአገልግሎቱ ስኬት ሆኖለታል፡፡

ሐዋርያው ጴጥሮስም ስለ አሕዛብ መዳንና ስለ ጳውሎስ አገልግሎት በኢየሩሳሌም በተደረገው ጉባኤ ላይ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለኛ ደግሞ እንደሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ (አህዛብ) መካከል አንዳች አልለየም፡፡” (የሐዋ.15፡8) በዚህ ሥፍራ የምናነበው የእግዚአብሔር ቃል ጳውሎስ ምን ያህል ለአሕዛብ የተሰጠ አገልጋይ መሆኑንና እግዚአብሔርም ምን ያህል እንደ ሚወዳቸው መንፈስ ቅዱሱን ለእነርሱም በመስጠቱ ያሳየናል፡፡  የጳውሎስ ልበ ሰፊነት ከተገለጠበት መንገድ አንዱ አሕዛቦችን ለአገልግሎት እየመረጠ መጠቀሙ ነው፡፡ ከተጠቀመባቸው አገልጋዮች ውስጥ ጥቂቶቹ ጢሞቲዎስ በአባቱ ግሪካዊ፣ (የሐዋ. 16፡1)፤ ቲቶ ሙሉ በሙሉ ግሪካዊ (ገላ.2፡3)፤ እና ሉቃስ ራሱም ይገኙበታል፡፡ ጌታ ለብዙ ነገር ጀማሪ አድርጎ ተጠቅሞበታል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን መባል፣ ሚስዮናዊ መባል፣ የሽምግልናን ሹመት በየከተማው ማደራጀትን በመጀመር ሁሉ ፈር ቀዳጅ ሆኖአል፡፡ እኛስ ጌታ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምን ተጠቀመብን?


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *