እነ ጳውሎስ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያገለገሉ ሳለ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ከደረሳቸው በኋላ ለወንጌል አገልግሎት ፈቃደኛ ሆነው ራሳቸውን ለይተው ሲውጡ፣ ሉቃስ በጽሑፉ ይተርክልናል፡፡
በምዕራፍ 13፡4 ላይ ስንመለከት፣ “እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ” ይላል፡፡ በመቀጠልም፣ ወደ ስልማናም ከዚያም ወደ ተለያዩ ከተማዎች እንደ ሄዱ እንመለከታለን፡፡ ምዕራፍ 13ን ስንመለከት፣ ከቦታ አመራረጥ፣ አቀራረብና ከስብከታቸው ይዘት ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ በርናባስ የቆጵሮስ ተወላጅ ስለ ነበረ፣ ከሚታወቅበት ከትውልድ አካባቢው አገልግሎታቸውን ጀመሩ፡፡ በመቀጠልም፣ ቁጥር 14-15 ላይ፡-“እነርሱ (እነጳውሎስ) ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኩራብ ገብተው ተቀመጡ፡፡ ሕግና ነብያትም ከተነበቡ በኋላ የምኩራብ አለቆች፡- ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው›› ይላል፡፡
እነጳውሎስም አገልግሎታቸውን የጀመሩት ሰዎች በቀላሉ በሚገኙበት በምኵራብ ነበር፣ ይህም ለኮሙዩኒኬሽን (ተግባቦት) አመቺ ስፍራ ነበረ፡፡ አገልግሎትም በሚሰጡበት ጊዜ ከሚያውቁት ተነስተው ወደ ማያውቁት በማምጣት ኢየሱስን ማስተዋወቅ ጀመሩ፡፡ ከብሉይ ኪዳን ጀምረው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በተረኩላቸው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጌታን አምነው ሊከተሉዋቸው ቻሉ፡፡ “በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ›› (ቁ.44)፡፡ ከአይሁድ ጀምረው ወደ አሕዛብ ዘወር እንዳሉም የሚቀጥሉት ጥቅሶች ያመለክቱናል፡፡
“የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፣ እነሆ፡- ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን፡፡”(ቁ.46) በማለት ያቀዱትን ይናገራሉ፡፡ ጳውሎስም ጌታ በተገናኘው ጊዜ የተናገረውን በማስታወስ እንዲህ ይላል፣ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ” (ቁ.47)፡፡ ይህንንም ሐሳብ አሕዛቦች ሰምተው የሰጡትን ምላሽ ስንመለከት እንደሚከተለው ሆኖ እንገኘዋለን፤ “አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፣ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ” (ቁ.48-49)፡፡ በመቀጠልም፣ በምዕራፍ 14 ላይም ስንመለከት፣ እንደ ለመዱት በምኵራብ በመገኘት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ “በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ” (14፡1)፡፡
መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው ሲሄዱ እንጂ፣ ቤተ ክርስቲያን መርሐ-ግብር (ፕሮግራም) አውጥታ ‹‹በዚህ ተቀመጡ፣ በዚህ ሂዱ›› እያለች ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ስትልካቸው አናይም፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ምሪት በሄዱበት ሥፍራ ሁሉ፣ ምንም እንኳን ተቃውሞ ቢደርስባቸውም፣ ውጤታማ ሲሆኑ እንመለከታለን፡፡ ውጤታማ በሆኑበት ሥፍራ ሁሉ እነርሱም በተለያዩ ከተሞች ወንጌልን እየሰበኩ ሽማግሌዎችን እየሾሙ ከከተማ ወደ ከተማ እየተዘዋወሩ መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው አገልግሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ላከቻቸው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ሕዝቡን ሰብስበው የመጀመሪያውን የወንጌል ጉዞ ዘገባ (ሪፖርት) አቀረቡ፡፡
“ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ፡፡ በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ፡፡ ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ” (14፡26-28)፡፡ እነርሱም የላከን መንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ ብለው ዘገባ አናቀርብም አላሉም፡፡ ብዙዎቻችን ብዙ ጊዜ ዘገባ ማድረግ አይሆንልንም፡፡ በተለይ በቃል ይሻለናል እንጂ፣ በወረቀት ዘገባ ማድረግ አለመድንም፣ ስለዚህ አንወደውም፡፡
አንዳንድ ለወንጌል ሥራ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደረጉ ድርጅቶች ዘገባ ደጋግመው ጠይቀው ሲያጡ፣ የሚሰጡትን የቀለብ ድጎማ ያቆማሉ፡፡ አንዳንድ ለወንጌል ሥራ የተሰማሩ አገልጋዮች ለነገሩ ዘገባ የሚያደርጉበት መንገድ የላቸውም፤ በፖስታ መላክና ስልክ መደወልም አይችሉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትንሽም ቢሆን የተንቀሳቃሽ ስልክ (የሞባይል) አገልግሎት ይሻላል፡፡ እርሱም ቢሆን ካርድ ካልተሞላላቸው በስተቀር መሙላቱ ለእነርሱ ከባድ እንደሚሆንባቸው ግን የታወቀ ነው፡፡ ሆነም ቀረ፣ በተንቀሳቃሽ ስልክ ዘገባ እየጠየቁ ለሚረዷቸው ድርጅቶች ሪፖርት የሚያደርጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉም አውቃለሁ፡፡
በሌላ ጎኑ፣ ‹‹እኔ የተላኩት በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ፣ ከጌታ በስተቀር ለማንም ዘገባ አላቀርብም›› የምንል አገልጋዮችም አንጠፋም፡፡ ዘገባ ለአንድ ነገር መከናወን ለሠሪውም ሆነ በገንዘብ ለሚደግፈው ዋና ማሰረጃ ነው፡፡ ግለሰቦችና አጥቢያዎች ከጳውሎስና ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ መስማታቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን መታዘዛቸው፣ በቡድን ሆነው ማገልገላቸው፣ ከሚታወቁበት አካባቢ መጀመራቸው፣ ምኲራብ መጠቀማቸው፣ ለተላኩበት አጥቢያ ዘገባ ማቅረባቸው ሁሉ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ያለው ልዩነት ምንም ችግር ሳይፈጥርባት የመንፈስ ቅዱስን ድምፅ እየሰማች አገልጋዮችን በመስጠት የወንጌል መልእክተኛ (ሚስዮናዊ) ላኪ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ማየት እንችላላን፡፡ እኛም በዘመናችን ሚስዮናዊ ላኪና ተላኪ እንድንሆን ጌታ ይርዳን፡፡
0 Comments