በቤተ ክርስቲያናችሁ ጌታን ማገልገል ፈልጋችሁ የሚያቀርባችሁ ሰው አጥታችሁ ታውቃላችሁ? በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ዘመድ ወይም ጓደኛ ካልሆናችሁ አገልግሎት ማግኘት አትችሉም፡፡ በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዕውቀት የምትበልጧቸው ከሆነ፣ ወደ አገልግሎት በተለይም ወደ መስበክ፣ ማስተማርና መሪነት በፍጹም ልትመጡ አትችሉም፣ ምክንያቱም ቦታችን ወይም ሥልጣናችን ይወሰዳል ብለው ስለሚያስቡ አንዳንዶቻችሁን ወደ አገልግሎት በፍጹም አያስጠጓችሁም፡፡ እናንተም በተራችሁ ያንኑ ታደርጉ ይሆናል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም ጌታ በኃይል ተገናኝቶት ወደ ድነት ከመጣ በኋላ፣ ራሱን አዘጋጅቶ ወደ አገልግሎት ሊገባ ሲል የሚያስጠጋው በማጣቱ ተቸግሮአል፡፡ እንኳን ለማገልገል ቀርቶ ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ኀብረት ለማድረግ መቅረብ አልቻለም፣ ምክንያቱም ጳውሎስን በአሳዳጅነቱ ያውቁት ስለ ነበረ ነው፡፡ የሰው ልጆች አንድ ጊዜ ያየነውን ውጫዊ ነገር በፍጹም አንረሳም፡፡ ስለዚህ ጳውሎስን የሚያውቁት በአሳዳጅነቱ እንጂ፣ በውስጣዊ ሕይወቱ ለውጥ እንዳገኘ ሰው አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ደረሰበት፡፡ ጳውሎስ ከተለወጠ በኋላ በደማስቆስ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን እንደኖረ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን አይሁድ ሊገድሉት እንዳሰቡ ደቀ መዛሙርት ባወቁ ጊዜ፣ በእነርሱ እርዳታ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ አደረጉት፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሳይሆንለት፣ የጠበቀው ችግር ነበር፡፡ የሐዋርያት ሥራ 9፡26 ላይ ሉቃስ እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል፡- “ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፣ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት፡፡”
በዚህ ጊዜ በሐዋርያት 9፡27 ላይ እንደምናገኘው፣ “በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ተናገረ ተረከላቸው፡፡”
ጳውሎስም፣ “በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ (ሐዋርያት) ጋር ነበረ” (ቁ.28)፡፡ በርናባስ ምንም እንኳን የማቀራረብ ሥራ ሠርቶ ቢሳካለትና ኅብረት እንዲያደርግ ቢያደርግም፣ ከግሪክ አገር የመጡ አይሁዶች ደግሞ ጳውሎስን ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ወንድሞች በቂሣርያ አድርገው ወደ ጠርሴስ እንዲሄድ አደረጉት፡፡
ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡26 ላይ፣ “…በወገኔ ፍርሃት በአሕዛብ ፍርሃት…” ብሎ የሚገልጸው ሀሳብ፣ ከመለወጡና አገልግሎት ከመጀመሩ እንደ ደረሰበት ማየት እንችላለን፡፡ በደርግ ጊዜ አንዳንድ አገልጋዮችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስማችን በሕዝብ ደህንነት በፀጥታ ክፍሉ ተመዝግቦ ይገኝ ስለ ነበረ እኛም እንደ ጳውሎስ በፍርሃት እንመላለስ ነበረ፡፡
ቀደም ብለን በምዕራፍ 8 እና 11 ላይ እንዳየነው፣ በሐዋርያት ላይ በደረሰው ስደት ምክንያት ተበትነው የነበሩት ወንድሞች ወንጌሉን በተለየዩ ከተማዎች አሰራጩት፡፡ በዚህ ጊዜ በአንጾኪያ ወንጌል የተሰበከላቸው ያመኑ ግሪኮች ነበሩ፣ ይህም ወሬው በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ ተሰማ፣ ሁኔታውን እንዲያጣራ በርናባስ ተልኮ በነበረበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ሥራ በማየቱ ደስ ብሎት፣ ጸንተው እንዲቆሙ መክሯቸው በመቀጠል ጳውሎስን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ እንደ ሄደ ቃሉ ይነግረናል፡፡
በሐዋርያት ሥራ 11፡25 ላይ፣ “በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው” ይለናል፡፡ ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያንም ጋር ሕብረት እንዲያደርግ ከረዳው በኋላ፣ አብረው ለአንድ ዓመት በሙሉ ቃሉን ሲያስተምሩ መቆየታቸውን ሉቃስ ይነግረናል፡፡
ዛሬም አንዳንዶቻችን በመለወጣችንና አገልግሎት በመጀመራችን፣ እንዲሁም ብዙ ዓመት ያገለገልን ብንሆንም፣ እንደ ጳውሎስ የሚያስጠጋን ልናጣ፣ ስደትና መከራ ሊገጥመን፣ ቀለብ ልናጣ እንችላለን፡፡ የጳውሎስ ችግር ከውስጥም ከውጭም ስለ ነበረ፣ ከእኛ ይልቅ በጣም ከባድ ያደርገዋል፡፡ ቢሆንም ግን በተለያየ ምክንያት ተቃውሞና ስደት ሊደርስብን ቢችልም፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ ደርግ ዘመን ችግር ሊያመጣብንና ሊያዘጋብን ይችላል ብለን አንፈራም፡፡ ምንም ነገር ይግጠመን፣ እንደ ጳውሎስ ጌታ ለአገልግሎቱ እንደጠራን ካወቅንና ከተረዳን ወደ ፊት እንጂ፣ ወደ ኋላ ልንል አይገባንም፡፡
ጌታም እንደ በርናባስ ያሉ ለአገልግሎት የሚያዘጋጁና የሚያጽናኑ ሰዎችን ይሰጠናል፡፡ እንደ በርናበስ ያሉ ልበ ሰፊዎች ደካሞችን እንደ ድካማቸው፣ ብርቱዎችንም እንደ ብርታታቸው የሚቀበሉ ያስፈልጉናል፡፡ በርናባስ መሬቱን ሸጦ ለጌታ አገልግሎት የሰጠ፣ (የሐዋ. 4፡36-37) ሰው ነበር፡፡ ሐዋርያት ሳውልን በፈሩት ጊዜ ወደ እነርሱ አቅርቦ ስለ ለውጡ በማስረዳት እንዲቀበሉት አድርጎአል፡፡ (9፡27) በመቀጠልም፣ ወደ አንጾኪያ ለአገልግሎት ሄዶ አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ እንደ ወጣና ባገኘውም ጊዜ ደስ እንዳለውና ወደ አንጾኪያ በማምጣት አገልግሎት እንዲጀምር ያደረገው እርሱ ነበር (11፡25-26)፡፡ ጳውሎስ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ አገልግሎት ባይሰጥ ኖሮ ምናልባት ወንጌል ለአሕዛብ መድረሱና መዳናችን አጠራጣሪ ይሆን ነበር፡፡
በሐዋርያት ሥራ 15፡36-41 ባለው ክፍል ውስጥ ጳውሎስ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ለአገለግሎት ይዤ አልወጣም ብሎ ከበርናባስ ጋር ክርክር ፈጥረው በነበረበት ጊዜ፣ በርናባስ ይዞት በመውጣት ለአገልግሎት እንዳዘጋጀው ቃሉ ይነግረናል፡፡ አንድ ጊዜ ጳውሎስ ማርቆስን አይጠቅመኝም ባለበት ጊዜና በተወው ጊዜ በርናባስ ከእርሱ ጋር ለወንጌል አገልግሎት ይዞት በመውጣቱና ታግሶ ማርቆስን በመያዙ፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በሚጽፍበት ጊዜ ማርቆስ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ቶሎ ና ብሎ ይነግረዋል (2ጢሞ.4፡11)፡፡ አንድ ጊዜ አይጠቅምም ብለን ያሰብነው ሰው በሌላ ጊዜ ደግሞ ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ ሰውን በትዕግስት ይዘን ወደ መንፈሳዊ ዕድገት፣ ብስለትና አገልግሎት ልናደርሰው ይገባናል፡፡ ዛሬም እንደ በርናባስ ያሉ አገልጋዮች ‹‹አንፈልጋችሁም›› ስንባል የሚፈልጉን፣ ለአገልግሎት የሚያዘጋጁንና የሚያበቁን ያስፈልጉናል፡፡ በአገልጋዮች መካከል ሰላም የሚፈጥሩ፣ የጠፉትንና የባዘኑትን የሚፈልጉ፣ በገንዘባቸውም ጭምር የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ጌታ እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል፡፡ ዛሬ ጌታ እንዲህ ዓይነት ሰው ቢፈልግ ማንን ያገኝ ይሆን? እንደ ኢሳይያስ ‹‹እኔን ላከኝ›› የሚልና ተልኮም ራሱን እንደ በርናባስ አዘጋጅቶ ጌታ እንዲጠቀምበት የሚያቀርብ ማነው? ስለዚህ ቆም ብለን ‹‹እኔን ማን ነው ለአገልግሎት ያበቃኝ?›› ‹‹እኔስ ማንን ላበቃ እችላለሁ?›› ብሎ መጠየቅና ተልዕኮው የት እንደ ደረሰ መፈተሹና ማወቁ አማራጭ የሌለው ርምጃ ነው፡፡
0 Comments