ሳውል ሳይወድ በግድ ወደ ጌታ መጥቶ ድነትን አገኘ፡፡ በገላትያ 1፡17-18 ላይ እንደሚናገረው፣ ወደ ዓረብ አገር 3 ዓመት ቆይቶ ከመጣ በኋላ በሐዋርያት ሥራ 9፡20 ላይ እንደምናየው ደግሞ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሁሉ መስበክ ጀመረ፡፡ ወደ አገልግሎትም ሲመጣ በቁጥር 26 ላይ እንደምናነበው፣ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በአሳዳጅነቱ ስለምታውቀው፣ እንኳንስ አገልግሎቱን መለወጡንም ልትቀበል አልቻለችም፡፡
በደርግ ዘመን ወታደሮች፣ ካድሬዎችና የፓርቲ አባል የነበሩ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ የሚያምናቸው አልነበረም፣ ምክንያቱም አሳልፈው ይሰጡናል ብለን ስለ ምናስብ ነበር፡፡ እንደ አሁኑ ጊዜ የአምልኮ ነጻነት አልነበረምና፣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትም ተዘግተው፣ አንዳንዶቻችንም በእስር ቤት ከ7 ወር እስከ 2 ዓመት ድረስ ትንሽ የቆይታ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ በየቦታውም የተገደሉ እንዳሉ የታወቀ ነው፤ እኔ ሁሉንም ባላውቅ፡፡ ከዚህ በላይ እንዳየነው፣ አንዳንድ ሰዎች ቀላል በሆነ መንገድ ወድደውና ፈደቅው ሳይሆን፣ ከአቅማቸው በላይ በሆነ ኃይል ተገደው ወደ ጌታ ይመጣሉ፡፡ እግዚአብሔር ሰዎችን በኃይልና በግድ እንዲለወጡ የሚያደርግበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡፡ ሰዎች ኃይሉንና ታላቅነቱን አይተው እንዲድኑበት ለማድረግ ነው፡፡ ለሥራውና ለአገልግሎቱ አስፈላጊ ሆነው ከተገኙ በማንኛውም መንገድ ተጠቅሞ ወደ እርሱ እንዲመጡ ሊያደርግና ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡
እግዚአብሔር በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ የተጠቀመባቸው ሦስት ዋና ነገሮች፡- (1) የሮማዊ ዜጋ መሆኑን፣ (2) የተማረ መሆኑን፣ እና (3) ልበ-ሰፊ መሆኑን ነበሩ፡፡ በአሁኑ ዘመን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ለመንቀሳቀስና ለመሄድ ቪዛ ያስፈልጋል፡፡ በደርግ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ ለመሄድ እንኳን ቪዛ ቀርቶ ፓስፖርት ለማግኘት እጅግ በጣም ትልቅ ችግር ነበር፡፡ ከአገር ውስጥ ገቢ፣ ከባንክ ከእያንዳንዱ ከሦስት ቦታ ክሊራንስ ካወጣን በኋላ ነበር ፓስፖርት የምናገኘው፣ ከዚያ በኋላ ወደ ቪዛ ክፍል ሄደን ነው መውጣት የምንችለው፡፡ አሁን ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፓስፖርት አውጥቶ በእጁ መያዝና በፈለገው ጊዜ ወደ ፈለገው አገር መሄድ ይችላል፡፡ ችግሩ ያለው ግን የምንሄድበት አገር ቪዛ በቀላሉ ሊሰጠን አይችልም፡፡ የምንሄድበት አገር ቪዛ ከሰጠን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ በአየር መንገድ ስንወጣ የመውጫ ቪዛ ይመታልንና ወደምንፈልገው አገር መሄድ እንችላለን፡፡
በጳውሎስ ዘመንም የሮማዊ ዜግነት ያለው ሁሉ እንደ ፓስፖርት ስለ ሚያገለግላቸው ከቦታ ወደ ቦታ፣ ከአገር ወደ አገር መዘዋወር ይችሉ ነበር፡፡ የሮም መንግሥትም 127 አገሮችን ይገዛ ስለ ነበረ፣ የሮም ዜግነት ያለው ሁሉ ያለ ምንም ሥጋትና ችግር ከስፍራ ስፍራ እንዲዘዋወሩ ፈቃድ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ የሮም ዜግነት እንዴት ይገኝ ነበር? የሮም ዜግነት በሁለት መንገድ ይገኝ ነበር፡፡ አንደኛው የሮም መንግሥት በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ታማኞች ለማግኘት ሲል በተወሰኑ ከተሞች ለሚወለዱ ሁሉ የሮማዊነት ዜግነት ይሰጥ ነበር፡፡ ጳውሎስም ይህ መብት በሚሰጥባት በጠርሴስ ከተማ ስለ ተወለደ፣ ይህን ዜግነት በትውልድ አገኘው፡፡ የመረመረው ሻለቃ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ እንዳገኘው ሲነግረው፣ ጳውሎስ ግን “ተወለድኩባት” ብሎ መለሰለት (የሐዋ.22፡28-29)፡፡ ሁለተኛ በብሔራዊ ውትድርና ለሚያገለግል ሁሉ ሲሰጥ፣ እንደ ሻለቃ ያለውም በሙስና በገንዘቡ አግኝቶት ነበር፡፡
ጳውሎስ ዜግነቱን ያገኘው በሙስና ሳይሆን፣ በውልደት እንዳገኘው ራሱ ተናግሮአል፡፡ የሙስና ነገር በዚያም ዘመን እንደነበር ስንመለከት፣ ዘመናት-ተሻጋሪ ችግር እንደሆነ መረዳት አያስቸግረንም፡፡ ይህ ከሰው ደም ጋር የተቆራኘውን ራስ ወዳድነት አንድ ሰው ከውስጡ ከራሱ ጋር ታግሎ መለወጥ አለብኝ ብሎ ራሱን አሸንፎ ካላስወገደ በስተቀር፣ ከውጭ በሚመጣ ግፊት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ተለወጥን፣ አዲስ ፍጥረት ነን የምንለውንም ሲፈታተነን እንገኛለን፡፡
በቅርቡ ለአገልግሎት ከአዲስ አበባ ወደ አንድ ሥፍራ ሄጄ በነበረበት ጊዜ አንድ አማኝ ወንድም ባለ ሥልጣን የነበረ የመሥሪያ ቤቱን ገንዘብ አጥፍቶ እንደታሰረ ሰማሁ፡፡ ከመታሰሩ በፊት ወንድሞች ይቅርብህ እያሉ መክረውት እንደነበረ ነገሩኝ፣ ነገር ግን አልሰማቸውም፡፡ “ንገረው ንገረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው” ይላሉ አባቶች ሲተርቱ፡፡ አሁን ከመከራው ተምሮ ይወጣል ብለው፣ መልካም የትምህርት ጊዜ እንዲሆንለት እየጸለዩለት ይገኛሉ፡፡
ጳውሎስ ያለሙስና ባገኘው የሮማዊ ዜግነት መብት በመጠቀም የሮም መንግሥት በሚገዛበት ስፍራ ሁሉ ከአገር ወደ አገር እየተዘዋወረ ወንጌልን መስበክ ችሎ ነበር፡፡
ሁለተኛው የጳውሎስ በግድ መለወጥ ያስፈለገው፣ እግዚአብሔር ሮማዊነቱን እንደ ተጠቀመበት ሁሉ የተማረ መሆኑንም ተጠቅሞበታል፡፡ እግዚአብሔር ባልተማሩም ሰዎች መጠቀም እንደሚችል በዘመናችን ያሉትን እናንተም እኔም የምናውቃቸው የእግዚአብሔር ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ይበልጥ በተማረ ሰው ለመጠቀም ፈልጎ ጳውሎስን የለወጠው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ጳውሎስ እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በማንበብና በመጻፍ ብቻ ሳይሆን፣ ብሉይ ኪዳንን፣ የአይሁድን ወግና ሥርዓት በታዋቂው አስተማሪ በገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረ ነበር፡፡
ስለ ጳውሎስ ይበልጥ ለማወቅ ፊልጵስዩስ 3፡2-11 ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ “እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ፡፡” በሥጋ መታመን ቢፈልግ፣ ከማንም የሚበልጥበት እንዳለው በቁጥር 4 ላይ ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር በተለይም ለአገልግሎት ሲጠራን አንድ ነገራችንን ሊጠቀምብን ፈልጎ እንደሆነ መረዳትና መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ትዕግሥታችንን፣ ፍቅራችንን፣ ልግስናችንን፣ ይቅር ባይነታችንን፣ ኅብረት ወዳድነታችንን፣ ታራቂነታችንን፣ ሰላማችንን፣ አስተዳደራችንን፣ ገንዘብ አያያዛችንን፣ ቆጣቢነታችንንና አዳማጭነታችንን፣ …ከእነዚህ በአንዱ ሊገለገልብን መርጦን ይሆናል፡፡ ጌታ ያለ ዓላማና ያለ ምክንያት እንዲሁ ለድነትና ለአገልግሎት አይጠራንምና፣ ለምን እንደጠራን ካላወቅን፣ በጸሎት ጌታን መጠየቅ አለብን፡፡ አዲስ ኪዳንን ስንመለከት፣ ጳውሎስ ሰፊውን የሚስዮናዊነትን አገልግሎት እንደሰጠና ብዙ መልእክቶችን እንደ ጻፈ እናውቃለን፡፡ የሉቃስም ትኩረት የሐዋርያት ሥራን ሲጽፍ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት አሕዛብ እንዴት በጳውሎስ አገልግሎት አማካይነት ወደ ድነት እንደመጡ መግለጽና መተረክ እንደሆነ አሳይቻለሁ፡፡ የብሉይ ኪዳን ዕውቀቱና በባሕሉ ግሪካዊ መሆኑ ለአገልግሎቱ እንደ ጠቀመው መረዳት ይቻላል፡፡
ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ባልተማሩ ሰዎች ሊጠቀም ይችላል፣ ይበልጥ ግን በተማሩ ሰዎች ይጠቀማል፡፡ ያልተማርን ባልተማሩም ይጠቀማል ብለን ወደ ስንፍና እንዳንሄድ፣ የተማርንም ስለ ተማርን ብቻ ጌታ ይጠቀምብናል ብለን እንዳናስብ፡፡ እንደ ጳውሎስ እውነተኛ ጥሪና የአገልግሎት ጸጋው እንዳንለን ልናረጋግጥ ይገባናል፡፡ ዕድል ስላገኘን ብቻ በመድረክ ላይ ወጥተን ማገልገሉ በቂ አይሆንም፡፡
ሦስተኛው የጳውሎስ መለወጥ ያስፈለገበት ምክንያት፣ እግዚአብሔር ሮማዊና የተማረ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ልበ ሰፊነቱንም ሊጠቀምበት ፈልጎ በግድ እንደ ለወጠው አይተናል፡፡ ጳውሎስም እንደሚናገረው፣ ልበ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከአይሁድ ጋር አይሁዳዊ፣ ከአህዛብ ጋር አህዛባዊ፣ ሕግ ካለው ጋር ሕግ እንዳለው፣ ሕግ ከሌለው ጋር ሕግ እንደሌለው፣ ከብርቱ ጋር ብርቱ፣ ከደካማ ጋር ደካማ እየሆነ ሌሎችን ለመጥቀም ሲል ያደረገውን ይናገራል፡፡ (1ቆሮ.9፡19-23)
በጳውሎስ መለወጥ ምክንያት የመጡትን ለውጦች በስፋት ስንመለከት፣ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአንድ ዓመት ሙሉ ከበርናባስ ጋር በመሆን ብዙ ሕዝብ እንዳስተማሩ፣ ደቀ መዛሙርት እንዳፈሩና ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን እንደ ተባሉ ወደ ፊት በስፋት እናያለን፡፡ በመቀጠልም የአንጾኪያ አማኞች ገንዘብ አዋጥተው በጳውሎስና በበርናባስ እጅ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙ ሽማግሌዎች ላኩት፡፡ እነርሱም በታማኝነት እንዳደረሱና ወደ አንጾኪያ እንደ ተመለሱ በሐዋርያት 12፡25 ላይ እናነብባለን፡፡ አይሁድንና አህዛብን የሚያቀራርብና ሰውን በሁለንተናው የማገልገል የልማት አገልግሎት እንደ ሰጡ እናያለን፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ያሉትን ለውጦች ስንመለከት፣ የጳውሎስ መለወጥ ለአሕዛብ መዳንና ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ሰው ነበረ ማለት እንችላለን፡፡
ዛሬ እያንዳንዳችን ወደ ጌታ ለምን መጣን? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እንደ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን፣ በመምጣታችን ቤተ ክርስቲያናችን ምን ያህል ተጠቀመች? አደገች? ሰፋች? በቤተ ክርስቲያን ምን ለውጥ አመጣን? ወይንስ ችግር-ፈጣሪዎች ሆንን? የአገልግሎት ሕይወታችን እንዴት ነው? ሰዎች ስማችንን የሚያነሡት በምን መልኩ ነው? የእርሱን ዓይን ከምናይ እያሉ ይሸሹናል፣ ወይስ በፊት ለፊት እያሞገሱን፣ ዘወር ሲሉ ያሙናል፣ ስማችንን ያጠፋሉ፣ እርሱ ብሎ አገልጋይ ይሉናል፣ በስውር በተሳለ ምላሳቸው ያርዱናል፣ ወይስ በእርሱ እዚህ ደረስን ብለው ጌታን ያመሰግናሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ላይረዱን ይችላሉ፣ ሰዎች ባይረዱንም ጌታ ይረዳናል፡፡ ጌታ ለምንና እንዴት እንደጠራን ያውቃል፣ እኛም እናውቃለን፣ ያላወቅን ካለን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ስለዚህ በተጠራንበት ዋና ነገር ላይ ትኩረት አድርገን እንደ ተሰጠን ጸጋ በቦታችንና እንደ ችሎታችን ጌታን እናገልግል፡፡ ያለ ቦታችን ስንቀመጥ ብዙ ነገር እናበላሻለንና ጌታ በሰጠን ቦታ ብቻ እንቀመጥ፡፡ ለምን እንደ ተጠራንና ቦታችንን ስናውቅ፣ ከሌሎች ጋር በሰላም እያገለገልን እንደ ጳውሎስ ውጤታማ አገልጋይ እንሆናለን፡፡
0 Comments