ምዕራፍ አንድ ታላቁ ተልዕኮ እና ምዕራፍ ሁለት ታላቁ ተልዕኮ በኢየሩሳሌም የሚለውን ጨርሰን፣ ምዕራፍ ሦስት ታላቁ ተልዕኮ በአንጾኪያ ወደ ወደሚለው ርዕስ መግባት ጀምረናል፡፡ ጌታ ተልዕኮውን ለደቀ መዛሙርቱ ሲሰጣቸው በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እና በዓለም ዳርቻ የሚል እንደ ነበረ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ተልዕኮን መዘንጋት በሚለው ርዕስ ሥርም እግዚኣብሔር በመጀመሪያው እቅዱ ጴጥሮስን ወደ አህዛብ የሚልክበትን መንገድ እንደቀየሰ ተመለከትን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በሁለተኛው ቅየሳው መሠረት፣ ሌላ ሰው እንዳስነሳ ከዚህ ቀጥሎ በስፋት እንመለከታለን፡፡ እርሱ በየዘመናቱ አንዳንድ ሰዎችን ለየት ባለ መንገድ ወደ እርሱ በመጥራት አገልጋይ ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ ወድደው ፈቅደው ሳይሆን፣ በግድ ተይዘው ነው የሚያምኑትና ወደ አገልግሎት የሚመጡት፡፡ ከእነርሱ በላይ የሆነ ኃይል ሲያስገድዳቸው ሳይወዱ በግድ እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ ከገቡበት በኋላ ግን ሕይወትን ጣፋጭ ሆኖ ያገኙታል፡፡ በመቀጠልም በሕይወታቸውና በአገልግሎታቸው ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ወደ ኋላ አይሉም፡፡
እግዚአብሔር በሐዋርያት 1፡8 ላይ ያለው ተልዕኮ ወደ ግቡ እንዲደርስ በቤተ ክርስቲያን ላይ የመጣውን ስደት ሊጠቀምበት እንደ ወደደ ባለፈው ተመልክተናል፡፡ በመቀጠልም ጴጥሮስን ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት በመላክ ጭምር፣ ወንጌል ወደ አሕዛብ እንዲደርስ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም፣ ብዙ ውጤት እንዳልተገኘ አይተናል፡፡ ስለዚህ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9 ላይ የምናገኘውን ሐዋርያው ጳውሎስን፣ አስቀድሞ ከመለወጡ በፊት ሳውል እየተባለ የሚጠራውን፣ ቤተ ክርስቲያን ለማሳደድ፣ ክርስቲያኖችን ለማሳሰር ከባለ ሥልጣናት የማሰሪያ ደብደቤ ተቀብሎ ወደ ኢየሩሳሌም አስሮ ለማምጣት ወደ ደማስቆስ ሲሄድ ጌታ በመንገድ ተገናኘው፡፡ በኢየሩሳሌም ያሉትን አሳስሮ ይጨርስ አይጨርስ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ቢሆንም ግን፣ ጳውሎስ ማነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከፊልጵስዩስ 3፡3-11 ያለውን እንመልከት፡፡
“እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የምንታመን እኛ የተገረዝን ነንና፡፡ እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ፡፡ …በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ትውልድ፣ ከብንያም ወገን፣ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፣ ስለ ሕግ ብትጠይቁ ፈሪሳዊ ነበርሁ፣ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፣ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፣ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠየይቁ፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ…” በማለት ከመለወጡ በፊት የነበረውን ሕይወት ይገልጻል፡፡ የሚቀጥለውም ጥቅስ አሳዳጅነቱን ያሳያል፡፡ የሐዋርያት ሥራ 9፡31 ላይ፣ “በይሁዳም ሁሉና በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ” የሚል ቃል እናነብባለን፡፡
በይሁዳና በሰማርያ ያሉትን ካዳረሰ በኋላ፣ ወደ ደማስቆስ እንደ ሄደ መረዳት እንችላለን፡፡ ሳውልም ለማሳደድ በመንገድ ላይ እያለ ያላሰበው አደጋ ገጠመው፤ ከእርሱና ሥልጣንን ከሰጡት በላይ ሥልጣን ያለው ብርቱና ኃይለኛ የሆነ ጌታ እንደ ገጠመው ቃሉ ይነግረናል፡፡ “ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ ሳውል ሳውል ስለ ምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ድምጽ ሰማ፡፡ “ጌታ ሆይ ማን ነህ?” አለው፡፡ እርሱም፣ “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፣ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል›› አለው፡፡ እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ “ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው፡፡” (የሐዋ.26፡14)
ጌታም፣ “ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል” አለው፡፡ (የሐዋ.9፡3-6) “የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” የሚለው አባባል በባሕላችን ስለሌለ ለእኛ ብዙ አይገባንም ይሆናል፣ ለጳውሎስ ግን በደንብ ይገባዋል፡፡ በእስራኤል አገር አንድ ወይፈን ወይም በሬ ለእርሻ ለመጠቀም ፈልገው ኃይለኛ፣ ተዋጊና ተራጋጭ ከሆነባቸው፣ ለመግራት አንድ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነበራቸው፡፡ ዘዴውም ከበሬው ከኋላ ጭኑ ሥር ሁለት የሾሉ ብረቶች በማስቀመጥ፣ በሬው ወደ ኋላ እራገጣለሁ ሲል ብረቶቹ ጭኑን ይወጉታል፡፡ ስለዚህ ሳይወድ በግድ ከመወጋት ይልቅ ቀንበሩን ይዞ ወደፊት መጎተትን ይመርጣል፡፡
ጳውሎስም ምንም ለሃይማኖቱ ቀናተኛ፣ ሟችና ኃይለኛ ቢሆንም፣ ከእርሱ በላይ ኃይለኛ ስላጋጠመው፣ እንደ በሬው ‹‹ማንቁርቱን ስለ ተያዘ›› ሊለወጥና ወደ አገልግሎት ሊመጣ ችሎአል፡፡ ከመሞት ሕይወት ይሻለኛል ብሎ አስቦና ፈቅዶ ወደ እምነት እንደመጣ እንመለከታለን፡፡ ራሱ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መለወጡ የተናገረውን ከፊልጵስዩስ መልእክቱ እንመለከታለን፡፡ “ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፣ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፣ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጉድፍ እቆጥራለሁ፡፡” (ፊል. 3፡9)፡፡ ምንም እንኳን የማይችለው ኃይል አግኝቶት ቢያምንም፣ ከመሞት ሕይወት ይሻለኛል ብሎ ጌታን መርጦ እንዳመነ መረዳት ይቻላል፡፡ ሕይወትን ባይፈልግ ኖሮ፣ መሞትን መርጦ ለእምነቱ እዚያው ደማስቆስ መንገድ ላይ ሞቶ ይቀር ነበር፡፡ በክርስቶስ የሚገኘውን ሕይወት ስለ መረጠ፣ ከስሕተቱ ተመልሶ የሚያሳድደውን ኢየሱስን መስበክና ተመለሶ ለክርስቶስ መሰደድ ጀመረ፡ ሰው ሁሉ በአንድ ዓይነት መንገድ አይጠራም፡፡ ጌታ አሳዳጅ የነበረውን ሳውልን ለአገልግሎት (አሕዛብን ለመድረስ) ስለ ፈለገው በኃይል ሊለውጠው ችሎአል፡፡ አንድ ጓደኛዬ ታሞ ለሞት ቀርቦ ሳለ፣ በጓደኛው አማካኝነት ወደ ጸሎት ቤት ተወስዶ በጌታ ስም ተጸልዮለት ተፈወሰ፡፡ አሁን በእግዚአብሔር ቤት ትልቅ አገልጋይ ሆኖ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ጌታ በሕመም ባይገናኘው ኖሮ ወደ ጌታ በሰላማዊ መንገድ መምጣት ይቸገር ነበር፡፡ እያንዳንዳችንን ጌታ እንዴት እንደ ተገናኘን እስቲ እናስብ፡፡ ጌታ ሁላችንንም የተገናኘበት መንገድ የተለያየና አስደናቂ ነው፡፡ በሰው፣ በትራክት፣ በሬድዮ፣ በመዝሙር፣ በመጽሐፍ እና በመሳሰሉት መንገዶች በመጠቀም የመስቀል ፍቅሩን አሳይቶ ጠርቶናል፡፡ በምንም መንገድ ወደ ጌታ እንምጣ ሁላችንም ጌታን የማገልገል ኃላፊነት አለብንና በተሰጠን ጸጋ በሀሳብ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በጸሎት፣ እና በመሳሰሉት ሁሉ ጌታን በታማኝነት እናገልግል፡፡ ጌታም ይረዳናል፡፡
0 Comments