ብዙ ጊዜ በእግዚብሔር ፈቃድ ላይ በብዙ ነገር ግራ ተጋብቻለሁ፣ በተለይም በጋብቻዬ ዙሪያ ጠይሟን ወይስ ቀይዋን፣ ወፍራሟን ወይስ ቀጭኗን፣ ረጅሟን ወይስ አጭሯን፣ ስል ወደ አሥር የሚደርሱትን በመዝገብ ስማቸውን ይዤ፣ በመጨረሻ ላይ ያገባኋት ከአሥሩ ውጭ የሆነችውን ልጅ ነው፡፡ በመቀጠልም፣ ስምንት ዓመት ያህል አብረን ከኖርን በኋላ፣ በጡት ካንሰር ምክንያት ወደ ጌታዋ ተሰበሰበች፡፡ ማንን ላግባ? ብዬ የተፈተንኩት አነሰና እንደገና መሞቷ ሌላ ከባድና አስቸጋሪ ፈተና ሆኖ ተጨመረልኝ፡፡ እጅግ ተበሳጨሁ፤ ምግብ ያለመብላት፣ እንቅልፍ ያለመተኛት፣ የመሳሰሉት ሁሉ በሕይወቴ ተፈራረቁብኝ፡፡ ሰው የሚያየው የውጪውን እንጂ የውስጡን ስላልሆነ፣ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊረዳላችሁ አይችልም፡፡ ስለዚህ እኔ ለሰው ደስተኛ እመስላለሁ፣ ውስጤ ግን ከመጠን በላይ ተጎድቷል፡፡ መቼ ይህ ብቻ፤ ባለቤቴ ከመሞቷ በፊት፣ የሰባት ዓመት ወንድ ልጄ በመኪና ተገጭቶ እርሱን በሆስፒታል እያስታመምኩት እያለ ነበር ባለቤቴ ያረፈቸው፡፡ በየዓይነቱ ፈተና ይሏችኋል ይሄ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በባለቤቴ ሞት ምክንያት፣ ‹‹እንደምትሞት እያወቅህ እንዳገባት ለምን ፈቀድህ?›› ብዬ ከአንድ ዓመት በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እንዴት ከባድና አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰው የውጭውን እንጂ የውስጡን ችግር አይረዳላችሁም፤ በተለይ አገልጋይ ከሆናችሁ ሁልጊዜ ማፅናናት ከእናንተ ይጠበቃል እንጂ፣ አገልጋይ የሚፈተን የሚቸገር ስለ ማይመስላቸው፣ እናንተን የሚያፅናና ሰው በፍፁም አታገኙም፡፡
በ2ኛ. ቆሮንቶስ 1፡3-11 ላይ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በእስያ በነበረ ጊዜ ስለ ደረሰበት መከራ ሲናገር፣ ‹‹በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፣ ወንድሞች ሆይ፡- ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቈርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፡-ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፣ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር፡፡›› አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን፣ ጾማችን ወደ መታበይ ስለሚያመጣን፣ ጌታ ዝም የሚልበት ጊዜ አለው፡፡ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት በእርሱ እንድንታመን ነው፡፡
እኔም፣ ከአንድ ዓመት የመነጫነጭ፣ ተስፋ የመቁረጥ፣ ከልብ ስብራትና ድቀት ውስጥ አስደናቂ በሆነ መንገድ ጌታ ወደ እኔ መጥቶ፣ በዚህ ቃል አስደናቂ በሆነ መንገድ ለስላሳና አስደሳች በሆነ ድምጹ አጽናናኝ፡፡ እርሱ ማጽናናት ይችልበታልና፤ ተጽናናሁኝ፡፡ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፡፡ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፣ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን፡፡” የሚለው ቃል ለጊዜው መራራ ቢሆንብኝም፣ አሁን ግን በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፉ ላሉ ሁሉ የመጽናናት ምክንያት መሆን ችያለሁ፣ ቃሉ እውነት ነው፣ የጌታ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
ፈተና አንድና ሁለት ጊዜ ብቻ ፈትኖን ቢያበቃ መልካም ነበር፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ እንደገና በአንድ ወንድ ልጄ ሞት ምክንያት ወደ ቤተ ሰባችን ከባድ ፈተና ስለ መጣ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ዙሪያ በሦስት ተከፈልን፡፡ አንዳንዶቻችን ‹‹እግዚአብሔር ልጃችንን ያለ ጊዜው ቀጠፈው (ወሰደው)›› ስንል፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ ‹‹ያ ክፉ ጠላታችን ሰይጣን ወሰደብን›› አልን፣ ግማሾቻችን ደግሞ ‹‹የልጃችን የራሱ ጥፋት ነው›› በማለት ተከፋፈልን፡፡ ምክንያቱም ልጃችን የሞተው በቀለበት መንገድ ላይ ሲዘል ነበረና፡፡ የገናን በዓል ከአስተማሪያቸው ጋር ለማክበር ስጦታ ገዝተው ሲመጡ በድልድይ መምጣት ሲገባቸው፣ ድልድዩ አጠገባቸው ሆኖ ሳለ፣ እነርሱ ግን ብረትና ግምብ አጥር ዘልለው ሲመለሱ ከአምስት ልጆች መካከል የእኔ ልጅ ብቻ በመኪና ተገጭቶ ሞተ፡፡ በዚህ ማንን ተጠያቂ ያደርጓል?
እንዳልኳችሁ፣ ቤተ ሰባችን በሦስት ሀሳቦች ተከፋፍለን ሳለ፣ ሊያጽናኑን የመጡት ከመቶ ዘጠናው የሚሆኑት፣ ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ተቀበሉት›› እያሉን ነበር ያጽናኑን፡፡ ይህ እንዴት ከባድ ፈተና እንደነበረ በቃላት ልገልጽላችሁ አልችልም፡፡ ምክንያቱም፣ ‹‹የጌታ ፈቃድ ነው›› የሚለው ሐሳብ የእግዚአብሔርን ፍቅር ያጠፋብናል፣ ሰይጣን ነው እንዳንል ሰይጣንን ከእግዚአብሔር በላይ ማግዘፍ ይሆንብናል፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ቤተ ሰባችን በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አለን፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ? በቤተ ሰባችሁ ተወያዩበት፡፡
ወደ ተሰየፈው ሐዋርያው ያዕቆብ ታሪክ እንመለስና ታሪኩን በጥሞና እንመልከተው፣ ቃሉን ረጋ ብለን ብንመለከተው፣ መልሱን ማግኘት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአቱ ቀጣው እንዳንል፣ ኃጢአት እንደ ሠራ ቃሉ አይነግረንም፡፡ ጠላት ያመጣበትን ፈተና እንደ ጴጥሮስ ማዳን ሲችል፣ በዚያ መከራ በመስዋዕትነት እንዲያልፍ የፈቀደው የወንጌሉ ሥራ መስፋፋት እንዲችልና ሌሎች ክርስቲቶኖች ከእርሱ ሕይወት ጽናትንና ዋጋ መክፈልን እንዲማሩ ፈልጎ ያደረገው ይመስለኛል፡፡
ቤተ ሰቦቹ ግን፣ “ምን ኃጢአት ሠርተን ይሆን? ወይም “እግዚአብሔር ምነው ጨከነብን?›› ብለው ራሳቸውን ሳያስጨንቁና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሳይገቡ አልቀሩም፡፡ ወይም “እግዚአብሔር ምነው በሰይጣን ላይ ኃይል አጣ እንዴ?” ብለው የእግዚአብሔርን ኃይል ሳይጠራጠሩ አልቀሩም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ሀሳብና ፈቃድ ቶሎ አይገባንም፣ እግዚአብሔር ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ግድ-የለሽና የሰው ችግር የማይገባው ነው ብለን ከተናገርን በኋላ፣ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” የሚለውንም የተስፋ ቃል የት አለ? የዮሐንስ ወንጌል 3፡16 ፍቅሩስ የት አለ? ብለን ከጠየቅንና ከተጠራጠርን በኋላ፣ በሕይወታችን ብዙ ውጣ ውረዶችንና መላላጦችን ካሳለፍን በኋላ ነው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንረዳው፡፡ ለማንኛውም የፈተናችን ምንጩ እግዚአብሔር ይሁን፣ ሰይጣን ወይም እኛው ራሳችን እንሁን ማወቁ ለመፍትሔው እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡
ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ስናነሳ ልናውቃቸው የሚገቡ ሦስት ዋና ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሕይወቴ እጅግ አድርገው ጠቅመውኛል፡፡ የመጀመሪያው በዘዳግም 29፡29 መሠረት ለእኛ የተገለጠውንና ሚስጢር የሆነውን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለ ጌታ ፈቃድ ስናስብ፣ ምንም የማናውቃቸውና እርግጠኞች የማንሆንባቸው ብዙ ነገሮች አሉ:: ማንን ማግባት፣ ምን መሥራት፣ የት አገር መኖር፣ ስንት ልጅ መውለድ፣ በሐኪም መረዳት፣ የመሳሰሉት ሲገጥሙን፣ ምን ማድረግ እንዳለብን እርግጠኞች አይደለንም፣ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ በአብዛኛው የምንወደውን፣ ደስ የሚለንንና የሚጠቅመንን ነገር ስናገኝ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ከማለት በስተቀር፣ መቶ በመቶ እርግጠኞች መሆን አንችልም፡፡
በዚህ ነገር ጌታም ተፈትኖበታል፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የታቀደ መሆኑን እያወቀ፣ ወደዚህ ዓለም ተልኮ መጥቶበት እያለ፣ ለሦስት ዓመት ተኩል ሲናገረው ቆይቶ፣ እውነተኛውና ትክክለኛው የመከራው ሰዓት ሲመጣ፤ “አባት ሆይ፣ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ…” ብሎ በሉቃስ ወንጌል 22:42 ላይ ጸለየ፡፡ የአባቱ ፈቃድ ምን እንደሆነ እያወቀ ይህን ጸሎት መጸለይ አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን እንደ እኛ ሰብዓዊ ሆኖ ስለመጣ ያቺ መራራ ጽዋ ከፊት ለፊቱ ስትደቀን ከእርሱ እንድታልፍ አባቱን ጠየቀ፡፡ የመጀመሪያውን ጸሎት ብቻ ጸልዮ ቢያቆም “ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ…” የሚለውን ባይጨምር ኖሮ፣ ጌታ ተሸናፊ ይሆን ነበር፡፡ እኛም በቃሉ ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ እያወቅን፣ ለሥጋችን ምቾት በሆነው ነገር ላይ መለመን አይገባንም፡፡ በቃሉ ግልጽ የሆነ ፈቃዱን ካላወቅን ቆም ብለን እግዚአብሔር ሚስጢሩን እንዲገልጥልን በጸሎት ፊቱን መፈለግ አለብን፡፡
ሁለተኛው የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚታወቀው በቃሉ ነው፡፡ በቃሉ የተገለጠው ነገር ምንም የሚያሻማ አይደለም፡፡ ስለዚህ በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እንዳለ መቀበልና መታዘዝ ይገባናል፡፡ ጌታም በቃሉ ሲናገር “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል…” (ዮሐ.14፡23)፣ “…ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” (15፡10) ብሏል፡፡ ቃሉ ጠላትህን ውደድ ካለ፣ ቃሉን ለመታዘዝ ኃይል እንድናገኝ መጸለይ እንችላለን እንጂ፣ እስቲ ልጸልይበት ብለን ሀሳብ የምናስለውጠው ግን አይሆንም፡፡
በሦስተኛ ልናደርገው የሚገባን ነገር ቢኖር፣ እርግጠኞች ባልሆንባቸው ነገሮች በደስታና በነፃነት ሆነን በቃሉ ብርሃንነት በእግዚአብሔር እርግጠኛነት ላይ ተደግፈን ልንወስን ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሚናገረው “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” ስለሚል፣ በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስም እኛን ወደ ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረስ ኃላፊነቱን ይወጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ በዚህ መልኩ ለማወቅ ጥረት ካደረግሁ በኋላ የተረዳሁትን ተረድቼ ቀሪውን ሚስጥር የሆነውነ ነገር ለጌታ በመተው ልጽናና ችያለሁ፡፡ የጌታ ስም የተባረከ ይሁን፡፡ ጸጋው ከመከራችን ሁሉ ስለሚበልጥ፣ በችግራችን ላይ በድል ያራምደናል፡፡ ጳውሎስም በሮሜ መልእክቱ እንዲህ ይላል፣ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? … ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቻለሁ›› (ሮሜ. 8፡35-39) ስለዚህ የእግዚአሔር ፈቃድ ከገባን መልካም ነው፤ ካልገባንም በእርሱ በመደገፍ ወደ ፍቅሩ ጥላ ሥር በመሆን መቆየት እንጂ፣ ከጌታ መለየት የለብንም፡፡ ቀስ በቀስ የፈተናችን ምንጭ ማን እንደሆነ እየገባን ሲመጣ፣ ያን ጊዜ ይበልጥ በሕይወታችን ደስተኞችና አሸናፊዎች እየሆንን እንመጣለን፡፡
0 Comments