የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት እናውቃለን? በእግዚአብሔር ፈቃድ ዙሪያ ስንት መጽሐፍ አንብበናል? ምን ያህል ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተነጋግረናል? የሚያረካ መልስ አግኝተን ይሆን? በግላችን፣ በቤተ ሰባችንና በአገራችን እየሆኑ ያሉት ነገሮች በማን ፈቃድ የሚሆኑ ናቸው? መራብና መጠማት፣ መደኽየትና መበልጸግ፣ መከራና ሞት፣ ራስን ሰቅሎ መሞት፣ በመኪና አደጋ መሞት፣ በዘራፊ መገደል፣ ለመሳሰሉት ሁሉ ተጠያቂው ማነው? የእግዚአብሔርን፣ የሰውንና የሰይጣንን ፈቃድ እንዴት መለየት እንችላለን? በእኛ ላይ ሥልጣን ያለው ማን ነው? ሰው ራሱን ሰቅሎ ሲሞት፣ በመኪና አደጋ ሲሞት፣ አንዳንዶቻችን እግዚአብሔር ፈረደበት ስንል አንዳንዶቻችን ደግሞ ሰይጣን አደረገው እንላለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ የራሱ ጥፋት ነው እንላለን፡፡ የእግዚአብሔር፣ የሰውና የሰይጣን ድርሻ ድብልቅልቅ ብሎ ያስቸገረን ስንቶች እንሆን? እነዚህ ሦስት ፈቃዶች እንዴት ነው የምናስታርቃቸው ወይም የምንለያቸው? የእግዚአብሔር፣ የሰውና የሰይጣን ፈቃድ በሕይወታችን እንዴት ነው የሚከናወኑት? በሕይወታችን ላይ ባለ ሥልጣን ማነው እግዚአብሔር፣ ሰይጣን ወይስ እኛው ራሳቸን?
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 ላይ ሁለት በጣም እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ ነገሮች ሲፈጸሙ እንመለከታለን፡፡ ይህም የሐዋርያትን ቤተ ክርስቲያን አማኞችን ያስጨነቀ፣ ያስያስቸገረ፣ ፈተና የሆነ አንድ ድርጊት በመፈጸሙ ነው፡፡ ድርጊቱም የሐዋርያው ያዕቆብ በሄሮድስ ሰይፍ መገደልና የጴጥሮስ ደግሞ ከሄሮድስ ሰይፍ (እሥራትና ሞት) ማምለጥ ነው፡፡ ያዕቆብ የሐዋርያው ዮሐንስ ወንድም ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ነበረ፡፡ በሁለቱ ሰዎች መካከል ለምን ልዩነት ተፈጠረ? እግዚአብሔር ያዕቆብን ይጠላል? ጴጥሮስን ይወደዋል ማለት ነው? እንዲያ ከሆነ፣ ከቃሉ ምን ማስረጃ አለን? ወይስ ሰይጣን ከእግዚአብሔር የበለጠ ኃይል ኖሮት ነው? ወይስ ያዕቆብ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት የመጣበት ነው? ኃጢአት እንደ ሠራ የሚናገር ክፍል ከቃሉ ውስጥ ማግኘት እንችል ይሆን? አቤት፣ እንዲህ ያለ ግራ የሚያጋባ ነገር በስንቶቻችን ሕይወት፣ ቤትና አገልግሎት አልፎ ይሆን?
አንድ ሰው በፈተናና በችግር ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የመከራው ምንጭ ማን እንደሆነ እንዴት ሊያውቅ ይችላል? የአብርሃም የልጅ ልጅ፣ የይስሐቅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ወንድሙንና አባቱን በማታለሉ ለደረሰበት ነገር ሁሉ ተጠያቂ ማንን ያደርግ ይሆን? ዮሴፍስ በወንድሞቹ ሲጠላና ሲሸጥ ማን ይሆን ተጠያቂ? ኢዮብስ ለደረሰበት መከራና ችግርስ? ሐዋርያት እንደ ስንዴ ለመበጠራቸውስ?
እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያውቃል፣ ከመወለዳችን በፊትና አሁን ያለንበትን ወደፊት የሚሆኑብንን ሁሉ ያውቃል፡፡ ለዚህ ምንም ጥርጥር የለንም፡፡ ነገር ግን ህመም፣ ኀዘን፣ ሞት፣ ጦርነት፣ ቤት ቃጠሎ፣ የመኪና አደጋ፣ ፍቺ፣ ከትምህርት መውደቅ፣ ከሥራ መባረር፣ ጎዳና ተዳዳሪነት የመሳሰሉት ሁሉ በሕይወታችን ሲያልፉ የእግዚአብሔርን አፍቃሪነት አላጠፉባችሁም? እነዚህን ነገሮች እንዴት ማስተናገድ ቻላችሁ? እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያውቃልና ሁሉንም ነገር እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን አመጣው ማለት ልዩነት አላቸው፡፡
አንዳንድ ጥቅሶችን ከአውዳቸው ነጥለን፣ ስንጠቀምባቸው፣ የቃሉን እውነት መረዳት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል 1፡3 ላይ ያለው ቃል፣ “ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” የሚለው ጥቅስ ራሱን ሰቅሎ ለሞተም፣ ሰክሮ መኪና ሲያሽከረክር ለሞተም፣ ሚስቱንም በገዛ ፈቃዱ ለሚፈታም፣ የምናደርገው ከሆነ የተሳሳተ መረዳት ይመስለኛል፡፡ ጥቅሱ የሚናገረው ፍጥረት ሁሉ፣ የሚታይ ይሁን የማይታይ፣ ትልቅ ይሁን ትንሽ፣ ሰው፣ እንሰሳትና ዕፀዋት ሁሉ በእርሱ መፈጠራቸውን የሚያመለክት ጥቅስ ነው እንጂ፣ ሰው በራሱ ፈቃድ የሚያደርገውንም ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጸመ ነው እያልን እርሱን መክሰስና መወንጀል የለብንም፡፡ ስለዚህ ሁሉን ነገር እንዲሆን ፈቀደ ወይም እርሱ አዞት ነው እያልን ተጠያቂ ማድረግና ኃላፊነቱን ከእኛ ላይ ማንሳቱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ወይም ሁሉንም ነገር ያደረገው ሰይጣን ነው ብለንም መደምደም የለብንም፡፡ ወይም ሁሉንም ነገር የማደርገው እኔ ነኝ ብለንም ራሳችንን ሁልጊዜ በትዕቢትም ላይ ማስቀመጥ ወይም ራሳችንን እየከሰስን ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡
ከእግዚአብሔር የሚመጣው ፈተና ወይም ፈቃድ ሰዎች እንዲለወጡ ለወንጌል ሥራ የሚያግዝ፣ እኛን በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድናድግ የሚረዳና ከክብር ወደ ክብር እንድንለወጥ የሚያደርግ እንጂ፣ የሚያጠፋን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን እንዲሆን የፈለገው ነገር ካለ አንድ ባሊ ሙሉ ዕንባ ብናነባ ጌታ በሕይወታችን የሚፈጽመውን ሳይፈጽምና ሳይሠራ ከፈተናችን እንድንወጣ አያደርገንም፡፡ ፈተናችን የሰይጣን ከሆነ፣ ሊጥለን ሊያጎሳቁለንና ሊያጠፋን ስለ ሆነ፣ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከአናንተም ይሸሻል፣ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል›› ባለው መሠረት ወደ እግዚአብሔር እየቀረብን አጥብቀን ልንዋጋው ይገባናል፡፡ (ያቆ.4፡7-8) እግዚአብሔርም እንደ አባትነቱ ይረዳናል፣ ይታደገናል፣ ድልን በጠላታችን ላይ ያጎናጽፈናል፡፡ ጴጥሮስም በመልእክቱ፣ “… በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” ይላል (1ኛ.ጴጥ.5፡9)፡፡ ጳውሎስም፣ “… ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ …” (ኤፌ.6፡13) በማለት ከጠላት የሚመጣውን ፈተና የምንቋቋምበትን ዘዴውን ሁሉም ጸሐፊዎች ይነግሩናል፡፡ ፈተናው የራሳችን ከሆነ፣ በመስቀሉ ሥር ወድቀን በንስሐ ራሳችንን ልናስተካክል ይገባናል፡፡ ፈተናው ከእግዚአብሔር ከሆነ፣ ራሳችንን ሳናስጨንቅ የሚያነሳበትን ቀን በትዕግስት መጠበቅ አለብን፡፡ ፈተናው ከሰይጣን ከሆነ፣ እግዚአብሔር ለዓላማው ካልፈቀደለት በስተቀር በእኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደ ሌለው አውቀን ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ ልንጠጋ ይገባናል፡፡ ፈተናችን እንደ ኢዮብ እግዚአብሔር ያመጣብን ይሆን፣ ወይስ እንደ ሐዋርያት ሰይጣን ያመጣብን፣ ወይስ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ያዕቆብ እኛው ራሳችን ያመጣነው ይሆን? ብለን መጠየቅና ምንጩን በትክክል ማወቅ ይጠበቅብናል፤ የችግሩን ምንጭ (ፈቃዱን) ካወቅነው፣ እርምጃ ለመውሰድና ወደ መፍትሔው ለመምጣት አንቸገርም፡፡
0 Comments