የሐዋርያት ችግር፣ የነብዩ ዮናስም ችግር ነበር፡፡ ዮናስ ወደ ነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር በሚላክበት ጊዜ ለመሄድ ፈቀደኛ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም (ነነዌ ማለት የአሶር ዋና ከተማ ነበረች)፣ አሶራውያን በጊዜው ለእስራኤል ጠላቶች ስለ ነበሩ፣ ጠላት ለሆነ ሕዝብ “እንዲጠፉ እንጂ እንዲድኑ አልፈልግም” ብሎ አልሄድም አለ፡፡ እግዚአብሔር ወደ “ነነዌ ሂድ ሲለው” እርሱ ወደ ጠርሴስ ኮበለለ፡፡ ባለመታዘዙ ምክንያት በዓሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ ተውጦ ሦስት ቀንና ሌሊት ከቆየ በኋላ፣ በዓሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ ሳይደቅና ሳይልም እግዚአብሔር ዓሣውን ትፋው ሲለው ወደ ውጭ ተፋው፡፡ በመጨረሻም ዮናስ በብዙ ማጉረምረም ሂድ ወደ ተባለበት ወደ ነነዌ ሄዶ፣ በንስሐ እንዲመለሱ ሰበከ፡፡ ሕዝቡም በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ እግዚአብሔርም ሕዝቡን እንደሚወድ በምሳሌ በቅል አስተማረው (ዮናስ 4፡9)፡፡  

ዮናስ በከተማይቱ የሚመጣባትን ለማየት ዳስ ሠርቶ ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አንዲት ቅል ጥላ እንድትሆነው አበቀለለት፣ ዮናስም በቅሊቱ መብቀል እጅግ ደስ አለው፡፡ ወዲያውኑ በነጋታው እግዚአብሔር ያበቀላትን ቅል በትል ተበልታ፣ እንድትደርቅ አደረገ፡፡ ዮናስም በፀሐይ ትኩሳት በተቃጠለ ጊዜ ‹‹ከሕይወት ሞት ይሻለኛል›› ብሎ ለራሱ ሞትን ፈለገ፡፡ “እግዚአብሔርም ዮናስን  በውኑ ስለዚች ቅል …ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን?  አለው፡፡ …እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ …ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው፡፡›› እግዚአብሔር አይሁድን እንደሚወድ አሕዛብንም ይወዳል፣ ምክንያቱም አሕዛብም የእጆቹ ሥራዎች ናቸውና፡፡ ኢየሱስም በመስቀል ላይ የሞተውና ደሙን ያፈሰሰው ለሕዝቦች ሁሉ ነው፡፡

 ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩት አይሁዶች ለረጅም ዘመናት ከኖሩበት ጎጂ ልማዳዊ ባህል ተላቀው መውጣት አቃታቸው ፡፡ በሐዋርያት ሥራ 11፡18 ላይ እንዳየነው፣ የጴጥሮስን ምሥክርነት ከሰሙ በኋላ ትንሽ ልባቸው የተነካ ይመስላል፡፡ በተግባር ግን ሊገልጡት ቢችሉ ኖሮ ጥሩ መነካት እንደሆነ ያስመሰክሩ ነበር፡፡ በተግባር ግን እንደ ትልቅ ተራራ ስለ ሆነባቸው፣ ስለ አሕዛብ ያላቸውን አመለካከት ሊለውጡ አልቻሉም፡፡  በዘመናት በሰው አእምሮ ውስጥ የገባ ጎጂ ልምምድ (ባህል) በቀላሉ አይወጣም፡፡ ለዚህ ነው ‹‹ባህል ሲያስር ከሰይጣን ይልቃል›› የሚባለው፡፡

  ከዚህም የተነሳ በገላትያ 2፡6-10 ያለውን ሐዋርያት በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ትልቅ ግድግዳ ሲያቆሙ እናያለን፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሁለቱ ጀርመኖች ለሁለት ተከፍለው እንዳይገናኙ በመካከላቸው በሽቦ የታጠረ ግንብ ተደርጎ በነበር ጊዜ፣ ቤተ ሰቦችና ዘመዳሞች የማይገናኙበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ እንዲሁም ሐዋርያት በዓይን የሚታይ ግንብ ባይገነቡም፣ የሐሳብ ግንብ አቁመው እነርሱ ወደ ተገረዙት አይሁድ ብቻ እንደሚሄዱ፣ እነጳውሎስ ደግሞ ወዳልተገረዙት አሕዛብ መሄድ እንደሚችሉ ተስማምተው እንደ ተለያዩ ቃሉ በግለጽ ያሳየናል፡፡

ጳውሎስም ሲገልው እንዲህ ይላል፣ “… አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ (ወዳልተገረዙት) እነርሱም ወደ ተገረዙት (አይሁድ) ይሄዱ ዘንድ ለእኔና በርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፡፡” (ገላ.2፡9) በገላትያ 2፡10 ላይ ደግሞ፣ “ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ፡፡” ይላል፡፡ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በድህነታቸው ርዳታ ያስፈልጋቸው ስለ ነበረ፣ ያንን ለማድረግ ተጋሁኝ በማለት ይገልጸዋል፡፡

 ሌሎቹ ሐዋርያት እሺ ችግራቸው ይሁን፣ ጴጥሮስ ግን ምን ነካው? ወደ ሳምራውያንና ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄዶ አገልግሎ የለም እንዴ? ዮሐንስስ የፍቅር ሰው አልነበረም እንዴ? ይህ ድርጊት እንዴት ተዋጠለት? አይ የሰው ነገር፣ ስንት አንበሳ ሲያጓራባቸው ያልተበገሩ ለዚች ትንሽ የስናፍጭ ቅንጣት ለምታክል ጎጂ ልማዳዊ ባህል ተጽዕኖ መሸነፋቸው ያሳዝናል! በነገራችን ላይ የባህል ጉልበት ከአንበሳ በልጦ የሰውን ሁለንተና የሚቆጣጠር ነው:: ባሕል ቀላል ተጽዕኖ እንደሌለው አውቃለሁ፣ ቢሆንም ግን ከኢየሱስ በላይ መሆን አልነበረበትም፡፡ ባሕል ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የማይጋጭ እስከ ሆነ ድረስ በሁለተኛ ደረጃ ሊቀመጥና ልንጠብቀው እንችላለን፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ባህል ከሆነ ግን፣ ልናስወግደው ይገባናል፡፡   

እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰብዓዊ (ሰው) ሆኖ እንዲመጣ ያደረገው የዓለም ሕዝብ በእርሱ አምኖ የዘላለም ሕይወት  እንዲኖረው ልኮት ሳለ፣ አደራው ወይም ታላቁ ተልዕኮ የተሰጣቸው በጌታ የተመረጡ፣ የተማሩና ለሦስት ዓመት ተኩል የሰለጠኑ ናቸው፡፡ እነርሱ እንዲህ ዓይነት ስሕተት ሲሠሩና ደካማ ነገር ሲታይባቸው፣ እንዲሁም ጌታ ሰውን ለማዳን የከፈለውን ዋጋ ሲያሳጡበት፣ ጌታ እጅግ ታላቅ ሀዘን ሳይሰማው አልቀረም፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ እንደ ተጸጸተ ይናገራል (ዘፍ.6፡6-7)፡፡ በዚህም ሥፍራ ማዘኑን ተጽፎ ባናገኝም፣ ተልዕኮው ባለመፈጸሙ ማዘኑን መረዳት አያዳግተንም፡፡ እኛስ ዛሬ እንደ ግለሰብና ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በወደቁበት ውድቀት ውስጥ እንገኝ ይሆን?  እነርሱ በወደቁበት ውድቀት ውስጥ ላንሆንና ላንያዝ እንችል ይሆናል፡፡ ቢሆንም ግን የወንጌሉን ሥራ ወይም ታላቁን ተልዕኮ በግልም በቡድንም በምናመልክበትም ቤተ ክርስቲያን እንዳንወጣ የሚያደርጉን ችግሮቻችን የተለያዩ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ችግሮቻችን ምንም ይሁኑ ምን፣ እግዚአብሔር ሲመለከተን የሚያዝንብን ነገር በሕይወታችን ይኖር ይሆን? ካለ ልንጸልይበትና ልናስወግደው ይገባናል፡፡ በምንም መልኩ ቢሆን በጎጂ ልማዳዊ ባሕላችን ምክንያት ወንጌሉን ልንዘነጋው ስለማይገባን፣ ከልማድ ተላቅቀን፣ ተልዕኮአችንን መፈተሽና ከግቡ እንዳልደረሰ አውቀን ከደረሰበት (ከኢየሩሳሌም) ወንጌሉን  ይዘን መውጣት ይኖርብናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *