እግዚአብሔር በኖህ ዘመን ምድርን በውኃ ባጠፋበት ጊዜ፣ ኖኅ ወደ መርከቡ ውስጥ ከአራዊት፣ ከእንሰሳትም፣ በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም፣ ከወፎችም ሁሉና ሥጋ ካላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት አድርጎ ወደ መርከብ ውስጥ ይዟቸው ገባ፡፡ ኖኅም ከጥፋት ውኃ ከዳነ በኋላ፣ ውኃው መጉደሉንና አለመጉደሉን እንድታይለት ቁራን ልኮአት ማረፊያ እየፈለገች በዚያው የውኃ ሽታ ሆና ቀረች:: ርግብን ሲልካት በመጀመሪያ ማረፊያ ስላጣች ዞራ ዞራ ተመለሰች፣ ሁለተኛ ሲልካት ቀኑን ሙሉ ውላ ወደ ማታ የወይራ ቅጠል ይዛለት መጣች፡፡ በሦስተኛም ጊዜ ሲልካት ተልዕኮዋን ሳትወጣና ተመልሳ ሳትመጣ ቀረች፡፡
በሐዋርያት ሥራ ላይ ወደ ምዕራፍ 11፡19 ላይ ሄደን ስንመለከት የምዕራፍ 8ን ቀጣይ ታሪክ እናገኛለን፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል፣ “በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፣ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር፡፡” ይህንን ጥቅስ ስንመለከት የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን የዘነጋች ትመስላለች፡፡ ጌታ የሰጣት ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜ እንዳላገኘና የወደቀችበትን ወይም ድካሟ የሆነውን ነገር ሉቃስ ሳይደብቅ ይነግረናል፡፡ ጌታ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ሂዱ ያለውን ታላቁን ተልዕኮ ለመሆኑ እንዴት ዘነጉት? የመዘንጋት ችግር ይሆን? ወይስ የተልዕኮው ዓላማ አልገባቸው ይሆን? ወይስ የተያዙበት ሌላ ወጥመድ(ጎጂ ልማዳዊ ባሕል) ይኖር ይሆን?
ወጥመዱም በአይሁድና በአህዛብ መካከል ያለው የባህልና የሙሴ ሕግ ልዩነት ነው፡፡ አይሁዶች ለረጅም ዘመናት የሙሴን ሕግ ይዘው የእግዚአብሔር ሕዝቦችና ወገኖች ነን በሚለው ሃሳብ ተይዘው ሲኩራሩበት ስለኖሩ፣ የአሕዛቦችን በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠራቸውን ረስተው የበታች አድርገው ማየታቸው፤ ሰዎች ምን ይሉናል በሚል ይሉኝታ ተይዘው፣ በጌታ የተሰጣቸውን ለሕዝቦች ሁሉ መድረስ ያለበትን ታላቁን ተልዕኮ ለማዳረስ የወገናዊነትን ቀንበር ሰብረው መውጣት አልቻሉም፡፡
የሰው ልጆች ስንባል በግብዝነት፣ በትዕቢት፣ በኩራትና በማስመሰል በቀላሉ እንያዛለን፡፡ ብዙ ጊዜ ሁላችንም ሟችና አፈር መሆናችንን እንረሳና ራሳችንን ከሌላው በቀለማችን፣ በዘራችን፣ በዕውቀታችንና በሀብታችን ስናበላልጥ እንገኛለን፡፡ ከአባቴ በምክር ከሰማኋቸው ሕይወቴን ከቀረፁኝ ንግግሮች አንዱ እንዲህ ይላል፡- “መለስ ቀለስ ብላ አየችው ቀሚሷን፣ እረሳችውና ከአፈር መቀየጧን፡፡” ይህን ምሰሌያዊ አነጋገር ከአባቴ ከልጅነት ጀምሮ እየሰማሁ ስለ አደግሁ፣ ወደ ትዳር ዓለም ስመጣ ከዘሬ ውጭ ነው ያገባሁት፡፡ ‹‹ከዘርህ ማግባት አለብህ›› እያለ ሁልጊዜ የሚመክረኝ አጎት ነበረኝ፡፡ ከዘሬ ውጭ ማግባቴን ሲያይ አኮረፈኝ፤ ሊያናግረኝ በፍጹም ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ማንኛውም ዘር ማለትም ነጭ፣ ጠይምና ጥቁር ቆዳ ያለው ሁሉ በስለት ቢበጣ (ቢቆረጥ) ሁሉም የሚወጣው ቀይ ደም ነው፡፡ ስለዚህ የበላይና የበታች አድርጎ የሚያበላልጠን ምንም ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔር ሁላችንንም እኩል አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ልዩነት የሚፈጥረው የተወለድንበት አካባቢ፣ ያለን ዕውቀት፣ ሀብትና አስተሳሰባችን ብቻ ከመሆኑ በስተቀር፣ የሰው ልጆች ሁሉ የመጣነው ከአንዱ ከአዳም ዘር ነው፡፡ ‹‹ኩራት ራት እንደማይሆን›› ሳናውቅ ብዙ ጊዜ እንቸገራለን፡፡ ሌላውን ንቀንና የበታች አድርገን የትም አንደርስም፤ እንደ ሂትለር (በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን አገር መሪ) ወደ አፈር ከመሄድ በስተቀር፡፡ ዛሬ ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበትና ነጭና ጥቁሩ እየተጋባ ባለበት ሁኔታ እኛ በዚህ በዘር፣ በቋንቋና በቀለም የምንለያይና ወንጌልን ማወጅ ለወገኔ ብቻ የምንል ከሆነ፣ ጌታ ሳያዝንብን አይቀርም፡፡ ከድነት ተጥለንና ተቆርጠን እንዳንገኝ፤ በሚቀጥለው ጥቅስ ራሳችንን መፈተሽና ማየቱ መልካም ነው፡፡
“በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያ ቀን ብዙዎች፡- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” (ማቴ.7፡21-23)፡፡ አንድ ጊዜ ከፈረንጆች ጋር አንድ አምስት ሆነን ለአገልግሎት ወደ አንድ ክልል ሄደን ወደ አንድ ቡና ቤት ጎራ ብለን ሻይ ለመጠጣት ፈልገን አስተናጋጆችን ለመስተናገድ ብንጠይቅ፣ የሚያናግረን ሰው አጣን፡፡ ከሳምንት በኋላ ስንመለስ በቋንቋቸው የሚያናግራቸው ሰው ይዘን ስለነበር እዚያው ቡና ቤት ገብተን ሻይ ጠጥተን ወጣን፡፡ የሚያሳዝነው፣ ቤቱ የአማኞች መሆኑ ነው፡፡ ቋንቋ ሰው ሲወለድ ከእናቱ ማህፀን ይዞት የሚወለደው ችሎታ ሳይሆን፣ ከተወለደ በኋላ ከቤተ ሰቡ (ከማህበረ ሰቡ) የሚማረው ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋ ሀሳብ ለሀሳብ እንድለዋወጥ የሚያደርግ መግባቢያ ነው፡፡ መናገር እየቻሉ አለመግባባት ሥራንና አገርን መበደል ነው፡፡ ሥራ ሥራ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ለትምህርት ተልኮ (ሄዶ) ሳለ፣ ትምህርቱ በእንግሊዝኛ ሲሰጥ፣ እኔ መናገር፣ መስማትና መማር ያለብኝ በቋንቋዬ በአማርኛ ነው ብሎ አልማርም ቢል የሚሰማው አይኖርም፤ ምርጫው መማር ወይም ጥሎ መምጣት ነው፡፡ ጥሎ ቢመጣ የሚጎዳው ራሱንና አገሩን ነው፡፡ ሰው በቋንቋ ተግባብቶ የሚፈልገውን ካላገኘ፣ የራስም የአገርም ጥቅምና ዕድገት ሊገኝ አይችልም፡፡ ቡና ቤትና ምግብ ቤት ከፍቶ በቋንቋዬ ካላናገሩኝ (መግባቢያ ቋንቋ እየተቻለ) አላስተናግድም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ እንዲሁም የከበረውን ወንጌል (ታላቁን ተልዕኮ) ይዘን ቋንቋዬን ለሚሰሙ ብቻ ነው መናገር ያለብኝ የምንል ከሆነ፣ ተልዕኮአችንን እንዳንረሳና የጌታን ልብ እንዳናሳዝን መጠንቀቅ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ለሁሉም ጌታ ይርዳን፡፡
0 Comments