እግዚአብሔር አፍ የሰጣችሁ እንድትናገሩበት ሲሆን፣ ‹‹ዝም በሉ አትናገሩ›› ብትባሉ ምን ይሰማችኋል? እኔ  በደርግ ዘመን በእስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ለመናር የተቸገርኩበት ሁኔታ አጋጥሞኝ ነበር፡፡ (የኮሚኒስት ዘመን ስለ ነበረ፣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል፣ ብዙ ክርስቲያኖችም ታስረዋል፣ መጽሐፍ ቅዱስም በእጅ ይዞ መሄድ አስቸጋሪ ነበረ፡፡) ከታሰርኩበት ቀበሌ ወደ ከፍተኛው ጽሕፈት ቤት ተወስጄ፣ ከተለያየ ሥፍራ የመጡ ወደ ሰባት የሚደርሱ ባለ ሥልጣናት ባሉበት እየተጠየቅሁ  የምናገረውን ነገር መስማት ስላልፈለጉ፣ አትናገር አሉኝ፡፡ እነርሱ የሚፈልጉት ያልሆንኩትን በግድ የሲ.አይ.ኤ አባል ነኝ እንድላቸው ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ያለውን እውነት ስናገር፣ በቃ አትናገር ይሉኝ ነበር፡፡ ሰዎች እውነትን መስማት ካልፈለጉ፣ በቃ አትናገሩ ይሏችኋል፡፡ ምክንያቱም እውነት ጆሮአቸውን ስለሚያሳክካቸው ነው፡፡ እየሰሙ እንዳልሰሙ፣ እያወቁ እንዳላወቁ ይሆናሉ፡፡

ደቀ መዛሙርትም የደረሰባቸው ይህን የመሰለ ችግር ነበር፣ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3 ላይ ያለው ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ አካል ጉዳተኛ የነበረውን ሰው በጌታ በኢየሱስ ስም ፈውሰውት ሙሉ ጤንነቱን ካገኘ በኋላ፣ ይህን ፈውስ ያመጣውን ወንጌል ለሕዝብ ስለ ሰበኩ እንዳይናገሩ ከልክለው ወደ እስር ቤት ጣሏቸው፡፡ በማግስቱም ከእስር ቤት አውጥተው፣ “በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ?” ብለው ጠየቁአቸው፡፡ ጴጥሮስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፡- “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፣ እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለ ተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደ ዳነ ብንመረምር እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሳው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደህና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፣ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የታውቀ ይሁን፡፡ እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው፡፡ መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፡፡” (የሐዋ.4፡8-12)

አለቆች፣ ሽማግሎችና ጻፎችም ተሰብስበው የሰሙትን እውነት መቀበል ቢቸገሩም፣ ሁኔታውን ለማገናዘብ ጥረት አድርገዋል፡፡ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ መሆናቸውን፣ ከኢየሱስ ጋርም እንደነበሩ አውቀዋል፡፡ የተፈወሰው ሰውም አብሯቸው ስለ ነበረ፣ የተደረገውም ተአምራት እውነት መሆኑን ተረድተዋል፡፡ ቢሆንም ግን፣ የእነዚህን ሰዎች እውነትና የተፈጸመውን ፈውስ መቀበል አልፈለጉም፡፡ ስለዚህ እነርሱን ወደ ውጭ አውጥተው ከተመካከሩ በኋላ፣ “ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው፡፡”

ጴጥሮስና ዮሐንስም ምንም ሳይፈሩ በአምላካቸው ታምነው አስደናቂ የሆነ ምላሽ ሰጡአቸው፡- “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቁረጡ፣ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” ብለው መለሱላቸው፡፡ (የሐዋ.4፡18-19) በዚህም ጊዜ ባለ ሥልጣኖቹ የሚያደርጉትን ስለ አጡ ዝተው ፈቱአቸው፡፡ ዓይኑን ባፈጠጠ እውነት ላይ ምንም ሊያደርጉ ባለ መቻላቸው እያዘኑ ለቀቁአቸው፡፡

ሐዋርያትም ከተፈቱ በኋላ ወደ ወገኖቻቸው ሄደው ሽማግሌዎች ያሉዋቸውን ሁሉ ለወንድሞች ከነገሩዋቸው በኋላ፣ በአንድ ልብ ሆነው በመጸለይ ጌታ በሕይወታቸው ይበልጥ እንዲጠቀምባቸውና ፈውስ እንዲያደርግ መጸለይ ጀመሩ፡፡ የሐዋርያት ሥራ 4፡29-30 ጸሎታቸውም ተቃዋሚዎቻቸውን እንዲያጠፋቸው ሳይሆን፣ ዛቻቸውን ብቻ እንዲመለከትላቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን ቃሉን በፍጹም ድፍረት ለመናገር እንዲችሉ እየጸለዩ ሳለ፣ መንፈስ ቅዱስ በድጋሚ በሁሉም ሞላባቸው፡፡

“ልዑል ጌታ ሆይ፣ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፣ … አሁንም፣ ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው፡፡ ለመፈወስ እጅህን ዘርጋ፤ በቅዱሱ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ድንቅና ታምራት አድርግ፡፡” ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ሥፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ፡፡ (የሐዋ.4፡24-31 አ.መ.ት)

የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ካለፈችበት የስደትና የመከራ ሕይወቷ ብዙ ልንማራቸው የሚገቡን ብርቱ ጎኖች አሉዋት፡፡ ችግር ሲገጥማቸው ወደ ሕግ መሄድ ተገቢ ቢሆንም፣ ቅድሚያ የሚሰጡት ወደ ጌታ ፊት መቅረብን ነበረ፡፡ እኛስ በችግራችን በቅድሚያ ወደ ማን ነው የምንሄደው? ወደ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ሕግ ወይስ ወደ ጌታ?

አንድ ድኻ አማኝና ባለጠጋ ገበሬ ጎን ለጎን እርሻ ነበራቸው፡፡ ድኻውም ሁልጊዜ ስለ ወንጌል እውነት ይነግረው ነበር፡፡ ባለጠጋውም በጥላቻ የድኻው ሰብል በሚደርስበት ጊዜ ከብት ይለቅበትና ያስበላበታል፡፡ ወደ ዳኛም ቢሄድ መፍትሔ ባለማግኘቱ፣ በዚህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ተቸገረ፡፡  በመጨረሻም ያገኘው መፍትሔ በፍቅር ለማሸነፍ ሌሊት ሌሊት እየተነሳ የባለጠጋውን እርሻ በመጀመሪያ ውኃ እያጠጣ፣ በኋላ የራሱን ማጠጣት ነበር፡፡ ይህንንም ለብዙ ቀን አደረገ፡፡ ባለጠጋውም ይህንን ድሪጊት ማን እንደሚፈጽመው ተደብቆ ያይ ነበር፡፡ በመጨረሻም እርሻውን ውኃ የሚያጠጣለት ያ ምስኪን ድኻው ገበሬ መሆኑን ሲያውቅ፣ ቤቱ ድረስ በመሄድ ላጠፋው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ጠይቆት፤ ለጌታ ሕይወቱን በመስጠት የክርስቶስ አማኝ ሆነ፡፡(ምንጭ ካስተማሪዬ ወ/ዊ ኬዳሞ ሜቻቶ) 

መዝሙረኛው በመዝሙሩ እንዲህ ይላል፣ “ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሳሁ፣ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? ረዳቴ ሰማይንና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው (መዝ.121፡1)፡፡    ዛሬስ እንደ ሐዋርያት አትናገሩ የሚል ችግር ቢገጥመን ወደ ማን ነው የምናየው፣ የምንሄደውስ? ለመሆኑ ዛሬ አትናገሩ የሚል ኃይል በአካባቢያችን ይኖር ይሆን? ማን ያውቃል? ከውስጥ ማንነትም ይሁን ከውጭ የሚመጣ ማንም ይሁን የእውነትን ቃል “አትናገር” የሚል ከሆነ፣ እንደ ሐዋርያት ወደ ጌታ በጸሎት እየቀረብን መልሳችን “እንናገራለን” መሆን አለበት፡፡ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆነ ሁሉ የእውነትን ቃል መናገር አለብን፡፡ ይህ ደግሞ በሕገ መንግሥታችንም የተቀመጠልን መብታችን ነው፡፡ የመናገር መብት ባልነበረበትም ጊዜ የኢየሱስን አዳኝነት እንናገር ነበር፣ አሁንም  ቢሆን የአዳኙን የእውነት ቃል ከመናገር ዝም አንልም፣ እንናገራለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *