የሐዋርያት ሥራ 3፡1-10 ላይ ስንመለከት እንደሚነግረን አንድ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ አካል ጉዳተኛ የነበረ ሰው መልካም በሚሉአት ደጅ የቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ በየቀኑ የሚያስቀምጡት በሽተኛ ነበረ፡፡ እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ለጸሎት ሲገቡ አይቶ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ትኩር ብሎ ተመልክቶት ወደ እኛ ተመልከት አለው፡፡ በሽተኛውም ምጽዋት የሚሰጡት መስሎት ወደ እነርሱ በጉጉት ዓይኑን አፍጥጦ ተመለከተ፤ ድኻ ምን ጊዜም ያለውን የሰው እጅ ስለሚጠብቅ፡፡ የሚበላ ነገር መስሎትም ምራቁ አፉን ሳይሞላው አልቀረም፤ ልብስና ሌላም ነገር ሳይሰጡኝ አይቀርም ብሎ ሳያስብም የቀረ አይመስለኝም፡፡
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ብርና ወርቅ የለኝም ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ” አለው (ቁ. 6)፡፡ አሁንም ለማኙ ምንም ነገር የለኝም የሚለውን ድምፅ ሲሰማ ተስፋ ሳይቆርጥና ምን ዓይነት ጨካኝ ሰው ነው ብሎ ሳያስብ አልቀረም፡፡ ደግሞም መልሶ፣ “ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ” ሲለው፣ የሞተውና የተሟጠጠው ተስፋው እንደገና ሳይለመልም አልቀረም፡፡ በዚህ ጊዜ ምን የከበረ ነገር ይሰጠኝ ይሆን ብሎ የተለየ ጉጉት ውስጥ ገብቶአል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጴጥሮስም ‹‹በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሳና ተመላለስ ሲለው›› ቀኝ እጁን ይዞ ሲያስነሳው እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጸና፣ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፡፡ እየተመላለሰም፣ እየዘለለም፣ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከሐዋርያት ጋር ወደ መቅደስ ገባ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ሲለምን አይተውት ስለነበረ መደነቅና መገረም ሞላባቸው፡፡
ይህ ተአምራት ኢየሱስ ከእነርሱ ከተለየ በኋላ ጌታ በእነርሱ እጅ ያደረገው የመጀመሪያ ድንቅ ሥራው ነው፡፡ በዚህም በተደረገው ፈውስ አማካኝነት ስለ ክርስቶስ በነቢያት የተነገረውን ሁሉ በመጥቀስ ምስክርነታቸውን አስተላለፉና ሰውዬውም ፈውሱን ያገኘው ከእግዚአብሔር በተላከው መሲህ አማካኝነት እንደሆነ አስረዱ፡፡ ፈውሱ በውኑም በሕልሙም ያላሰበው ድንቅ ስጦታ ሆነለት፡፡
ዛሬ በግልም በቡድንም በምናመልክባት ቤተ ክርስቲያን ደረጃ የእኛን ርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ምን እያደረግን ነው? ከዚህ በፊት በቤታችን አካባቢና በመንገዳችን ከገጠሙን እንጂ፣ በቤተ ክርስቲያናችን አካባቢ በፍፁም አይገኙም ነበር፤ ቢመጡም እንደምንሰጣቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምክንያቱም በመስጠት ጽድቅ የለም ብለን ስለምናስብና፣ የምንሰጣቸውም ሳንቲም የትም አያደርሳቸውም ብለን ስለምንገምት ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ እያየን ምላሻችን ምን ይሆን? እንደ ሐዋርያት ተዓምራት የማድረጉ ስጦታ ባይኖረንም፣ በእጃችን ላይ ያለውን ነገር ማካፈል/መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ በእጃችን ላይ ምን አለ? መስጠት ያለብን ብር ብቻ አይደለም፡፡ በተለያየ መንገድና ሁኔታ መርዳት እንችላለን፡፡
እኔ በብር ሰዎችን መርዳት ባልችልም በሌላ ነገር መርዳት እችላለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ለአገልግሎት ወደ ክፍለ ሀገር ወጣ ብዬ ስመለስ፣ በቤታችን ሦስት ልጆች ያላትን እህት ባለቤቴ ቤት ውስጥ እንድትቀመጥ ፈቅዳላት አገኘሁ፡፡ እኔም በነገሩ ተስማምቼ ለአንድ ዓመት በቤታችን ተቀመጠች፡፡ በዚህ ጊዜ ለቤታችን በረከት ሆነልን፡፡ በመቀጠልም ከዚህ በመማር በቤታችን ውስጥ ወደ አምስት የሚጠጉ መጠለያ ያጡትን ሰዎች በተለያየ ጊዜ በማስጠጋት ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት እንዲኖሩ በማድረግ መርዳት ችለናል፡፡ በዚህ ጊዜ ያላመኑ ዘመዶቼና አማኞች ‹‹ኪራይ አስከፍል እንጂ በነፃ አታሰቀምጥ›› እያሉ ሀሳብ ይሰጡኝ ነበር፡፡ እኔም ገንዘብ ለጊዜው ቢጠቅምም ጠፊ ነው፣ ሰውን ማትረፍ ግን የዘላለም ሀብት ነው በማለት ሐሳቡን አልተቀበልኩትም፡፡ ሁላችንም ባለን ብንረዳዳ ችግረኛ ከመካከላችን ይጠፋ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ በነጻ ባናስቀምጥም የቤት ኪራይ እንኳን በመቀነስና በሌሎችም ጉዳዮች መረዳዳት ይቻላል፡፡ ዋጋችንን ከሰው ባናገኘው ከጌታ ዘንድ እናገኘዋለን፡፡
የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በግልም በቡድንም ያላቸውን የሚሰጡ እንደ ነበረና የሌላቸውን ይረዱ እንደነበረ ማየት እንችላለን፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕ.4፡34 ላይ፣ በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና በማለት በመካከላቸው የነበረውን መተሳሰብና ሕብረት ያሳየናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 11፡29 ላይ እንደምንመለከተው፣ እነርሱም ራሳቸው ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን እርዳታ የሚሰጣቸው ቢሆንም እንኳን፣ ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን የሚረዱ እንደነበሩ ማየት እንችላለን፡፡ እነዚህ ሁለት ሐሳቦች የሚቃረኑ ይመስላሉ፣ በይሁዳ የሚኖሩ አማኞች ድኾች ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለም፣ ነገር ግን የሚያገኟትን እየተከፋፈሉ ስለሚኖሩ፣ በመካከላቸው ምንም ችግረኛ አልነበረም በማለት ቃሉ ይገልጸዋል፡፡
የዕብራውያን ጸሐፊም፣ “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ›› ይላል (ዕብ.13፡16)፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ባለው የልጆች አገልግሎት ውስጥ ከብዙዎች መካከል አንድ በጣም ያስደነቀችኝ የአንዲት በዕድሜ የገፋች (አሮጊት) ሴት ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ ይህች ሴት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አንዲት 6 ዓመት የሚሆናት ሴት ልጅ ትረዳ ነበረ፡፡ በየወሩ 10 ዶላር ትልክላታለች፡፡ ሴትየዋም በዕድሜ ገፋ ያለች ስለነበረች፣ በየወሩ ከምትልከው ዶላር ሌላ ቆጥባ፣ “ሳልሞት ልጄን ልይ” ብላ ከውጭ አገር ኢትዮጵያ ድረስ መጥታ አይታት ሄደች፡፡
የመርዳቷ ሲገርመኝ፣ እዚህ ድረስ መጥታ ለማየት የወሰደችው ርምጃ ከአእምሮዬ በላይ ሆነብኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሴትዋ ሥራ የላትም፣ የምትኖረው መሬት የወዳደቀ የምግብና የመጠጥ ጣሳ ቆርቆሮ እየሰበሰበች በመሸጥ ነበር፡፡ አይገርማችሁም!
እንደ ግለሰብና ቤተ ክርስቲያን የት ነው ያለነው ? ምን እየሰራን ነው ? የእኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በዙሪያችን የሉም? በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በረንዳ አጥተው በየጎዳናው ላይ የሚውሉና የሚያድሩ ስንት ናቸው? ይህን ክፍል ከጻፍኩኝ በኋላ ምሳ እየበላን እያለ አንድ ወንድም አንድ ታረክ አጫወተኝ፡፡ አንድ ክርስቲያን ወንድም በጣም ርቦት የሚበላውን አጥቶ በምሳ ሰዓት ላይ ተነስቶ አንድ ቤተ ሰብ ዘንድ ሲሄድ፣ ምሳ እየበሉ ይደርሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎቹ እንግዳ መጣብን ብለው የሚበሉበትን ሳህን ሲያነሱት ሳለ፣ ትንሽ የእንጀራ ቁራሽ ተንጠልጥላ ሲያያት ያችን እንኳን ለመብላት እየተመኘ እያለ ተንጠልጥላ የነበረችው የእንጀራ ቁራሽ ስትወድቅ ውሻ በላትና አረፈው፡፡
ስንቶች ይሆኑ በዚህ ሁኔታ በእኛ አካባቢ የሚገኙ፣ መነሻ የሆነን ጴጥሮስ ነው፡፡ ‹‹ብርና ወርቅ የለኝም፣ ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ›› ብሎ፣ ብርና ወርቅ ሊያስገኝለት የማይችለውን ታላቅ ስጦታ ሰጠው፡፡ ዛሬስ እኛ የምንሰጠው ምን አለን ?
አሁን ይህን ጽሑፍ ልጽፍ የቻልኩት፣ ለወንጌል አገልግሎት ቅን ልብ ባላቸው ወንድሞች በተደረገልኝ መልካም ችሮታ፣ የራሴን ኮምፒውተር በመግዛትና መጻፍ በመጀመሬ እናንተንም ማገልገል ችዬአለሁ፡፡ ጌታ የደገፉኝን ወገኖች እንዲባርካቸውና ይህን ጽሑፍ ጌታ ተጠቅሞበት፣ የአንባቢ ሕይወት እንዲለወጥበት ጸሎቴ ነው፡፡ ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን፡፡ እኛም ለወንጌል ሥራ ቀንና ማታ ይሮጣሉ ለምንላቸው ወገኖች፣ ብንደግፍ፣ ብዙ ዕንቁ የሆኑ የተደበቁ ነገሮች ይወጣሉ፡፡ በየመንገዱም ወድቀው ለምናያቸው ከቁራሽ እንጀራ አልፈን በመተባበር ራሳቸውን የሚረዱበትንና የሚቋቋሙበትን ብናደርግ፣ እግዚአብሔር ይከብራል፣ ወንጌልም ተቀባይነት ያገኛል፡፡ እኛም በጌታ ዘንድ ዋጋ እናገኝበታለን፡፡
0 Comments