በኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት፣ ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣ የመጀመሪያው ፍጻሜ ያገኘው በባቢሎን ምርኮ ጊዜ እንደ ነበረ ተመልክተናል፡፡ እንደገና በ70 ዓ.ም የአይሁድ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንደምትወድቅ ስላወቀና ትንቢቱ እንደሚፈጸምባት ስለተረዳ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብዓዊ ሆኖ በመጣ ጊዜ ለኢየሩሳሌም ዘመድ እንደሞተበት ሰው እንዳለቀሰላት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ (ሉቃ.13፡31-35፤ 19፡41-44) አሁንም የአይሁድ ሕዝብ የሰላማቸውን ጌታ የሆነውን ኢየሱስን አልተቀበሉትም፡፡ ስለዚህ በዓለ ኀምሳ ወይም የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ተስፋ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፍርድ ጭምር ይዞ ነው የመጣው፡፡

ሉቃስ በወንጌሉ እንደሚነግረን፣ “… በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል …” ይለናል (ሉቃ.3፡16)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ እሳት መንፃትንና ፍርድን ያመለክታል፡፡ ለሐዋርያት የተገባው የተስፋ ቃል ወይም መንፈስ ቅዱስ ለአገልግሎታቸው ኃይል ሲሆንላቸው፣ ለማያምኑት አይሁድ ደግሞ ፍርድ ሆኖባቸው ነበር፡፡  

 እግዚአብሔር ሐዋርያትን በማያውቁት ቋንቋ ሲያናግራቸው በዚያ በበዓለ ኀምሳ ቀን ለተሰበሰቡት ሕዝቦች ሁሉ፣ በተለይም በስደት ሄደው በተወለዱበት አገር ቋንቋ ሁሉም የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ይሰሙ ነበር፡፡ ልሳኑን የሚናገሩት ሰዎች በገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብለው ያልተማሩ፣ ብዙ ዕውቀት የሌላቸው፣ ማንም ሥፍራ የማይሰጣቸው ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በሐዋርያት ላይ በመገለጡ ምክንያት ብዙ ሰዎች ወደ ጌታ ሊመጡ ችለዋል፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ ከአዕምሮ በላይ ነበረ፡፡ ያዩት አውሎ ነፋስ፣ የሰሙት ድምጽ፣ እንደ እሳት የተቀመጡባቸው ልሳኖች በሰዎች ሊደረጉ የማይችሉ ነበሩ፡፡ ለእነርሱ ባይገባቸውም ለሚሰሟቸው ግን ግልጽ መልዕክት ተላልፎላቸዋል፡፡ 

“ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምጽ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፣ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ፡፡ ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፡- እነሆ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?” (ሐዋ. 2፡5-8) መልእክቱ የተላላፈው በሚገባቸው ቋንቋ ስለ ሆነ፣ ግልጽ ነበር፡፡ መልእክቱ ግን ምን እንደሆነ ተጽፎ አናገኘውም፡፡ እነርሱ ግን የእግዚአብሔርን  ሀሳብ በሚገባ ሰምተውታል፣ ግን አልተቀበሉትም፣ አልታዘዙትም፡፡    በተለያየ ቋንቋ የተላለፈው መልእክት ስላልተጻፈልን ምን እንደሆነ  አናውቀውም እንጂ፣ እግዚአብሔር ስለ ገባላቸው የተስፋ ቃል ፍጻሜና ስለሚመጣው ፍርድ በሰፊው ሳይናገራቸው አልቀረም ብዬ አስባለሁ፡፡ “ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ” በተባሉት መሠረት ሲጠብቁ ሳለ፣ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በተለያዩ ልሳኖች መናገራቸው አስደናቂ የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡ የዚህን ድንቅ ሥራ መልእክት በገዛ ቋንቋቸው ቢሰሙም ግን፣ ከ3000 ሰዎች ውጭ ያሉት የሰሙትን መልእክት አልተቀበሉትም፡፡ የሰሙት መልእክት ለግማሾቹ ለድነት/ለደህንነት ሲሆን፣ ለብዙዎች ደግሞ ለጥፋት ሆኖባቸዋል፡፡ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› ማለት ይሄ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ የአይሁድ ሕዝብ ለቅጣት በሮማውያን እጅ አልፈው ተሰጡ፡፡ በ70 ዓ.ም ጀኔራል ቲቶ/ታይተስ የተባለው የሮም ወታደር መጥቶ የኢየሩሳሌምን ከተማ ከብቦ በእሳት አቃጠላት፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል አለመስማትና አለመታዘዝ ውጤቱ ቅጣት ነው፡፡ ጌታም ያለቀሰላት ወደዚህ ፍርድ እንዳትገባ ነበረ፡፡

 በማቴዎስ 27፡25 ላይ እንደምናገኘው፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን “እንዳሉት ሆነባቸው፡፡ ጳውሎስ 1ኛ.ቆሮንቶስ 14፡21 ላይ የሚናገረው ይህንኑ ሀሳብ ነው፣ በሕግም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች በባዕዳንም አንደበት፣ ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም” (አ.መ.ት) ይላል ጌታ፡፡    

የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ነገሮች የተከፋፈለች ነበረች፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋናነት የተከፋፈሉት በልሳንና በትንቢት ስጦታዎች ነበረ፡፡ “የእኔ ይበልጣል” ”የእኔ ይበልጣል” በመባባል ነበር፡፡ ባለ ልሳኖቹ “የኛ ስጦታ ይበልጣል” ሲሉ ባለ ትንቢቶቹ ደግሞ “የእናንተ ስለማይታወቅ የእኛ የሚታወቀው ይበልጣል” በማለት ተለያይተው ስለ ነበር፣ ያንን ለማስተካከል ሲል እንዲህ በማለት ያስተምራቸዋል፣

“ወንድሞች ሆይ፣ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፣ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ፡፡ ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎችና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ፣ እንዲህም ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ ተብሎ በሕግ ተጽፏል፡፡” (1ኛ.ቆሮ.14፡20-21) በማለት የኢሳይያስን ትንቢት በመጥቀስ በበዓለ ኀምሳ ቀን በተለያየ ቋንቋ የእግዚአብሔርን መልእክት ሰምተው ወደ እግዚአብሔር ፍርድ እንደ ገቡት፣ እነርሱም እንዳይገቡ በማስጠንቀቅ ያሳስባቸዋል፡፡

አሁንም እናንተ ወደ ፍርድ እንዳትገቡ ተቀባብላችሁና ተከባብራችሁ በተሰጣችሁ የጸጋ ስጦታ ጌታን አገልግሉ በማለት ከስጦታዎች ሁሉ ለይቶና ሰፋ ባለ መንገድ ለሁለቱ ስጦታዎች ሰፊ ሥፍራ (3 ምዕራፎች) በመስጠት አስተምሯቸዋል፡፡ የጸጋ ስጦታዎች የተሰጡን የወንጌሉን ሥራ ለመሥራት፣ መንግሥቱን ለማስፋፋት እንጂ፣ ‹‹ይህ የጸጋ ስጦታ አለን!›› እያልን ራሳችንን ልናኩራራበት፣ ልንጣላበትና ልንከፋፈልበት አይደለም ፡፡  ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከተቀበሉ በኋላ፣ ያገኙትን በረከት ለአሕዛብ (ሕዝቦች) ለማካፈል ፈቃደኞች  መሆን አለመሆናቸውን በሰፊው እንመለከታለን፡፡ እኛስ የተቀበልነውን የጸጋ ስጦታ ልሳን፣ ትንቢት፣ ፈውስ፣ መናፍስት መለየት፣ እና የመሳሰሉትን ሁሉ ሌሎችን ለማገልገል እየተጠቀምንበት ነው ወይስ ራሳችን እየተገለገልንበት እንኩራራበታለን? የተሰጡን ስጦታዎች ለፍርድ እንዳይሆኑብን ልንጠነቀቅና ተልዕኮአችንን ልንፈትሽ ይገባናል፡፡ በተለይም እንደ ቆሮንቶስ አማኞች በስጦታዎች እየተወዳደርንና እየተቀናናን እንዳንጠፋፋ እንጠንቀቅ፡፡ የበዓለ ኀምሳን መልእክት ያልተቀበሉ ወደ ፍርድ ሲገቡ፣ መልዕክቱን የተቀበሉ በዚያ ፍርድ ውስጥ ሆነው ወንጌሉን ይዘው ለምስክርነት ወጡ፡፡ እስራኤላውያን በግብጽ በነበሩበት ጊዜ በመቅሰፍቱ ውስጥ እንዳለፉ፣ ሐዋርያትም በፍርዱ ውስጥ ሆነው ወንጌሉን ይዘው ወደ ጠፉት ወጡ፣ ጌታም ረዳቸው፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *