ጴጥሮስ ሕይወት-ለዋጭ ስብከቱን ኢየሱስን ማዕከል በማድረግ ያቀርበዋል፤  “የእሥራኤል ሰዎች ሆይ ይህን ቃል ስሙ፣ ራሳችሁ እንደምታውቁት የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተዓምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፡፡”… “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን  እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእሥራኤል ወገን ሁሉ ይወቅ፤” ብሎ ዋናውን ቁም ነገር ለሕዝቡ አስጨበጠ፡፡ (የሐዋ.2፡22 ፣36) ሕዝቡም ይህን ስብከት ከሰሙ በኋላ በቁ. 37 ላይ ‹‹ወንድሞች ሆይ፡- ምን እናድርግ?›› ብለው የሰጡትን ምላሽ እናገኛለን፡፡ ጐላ ብለው ያሉትን ቃላት በጥልቀት እንመልከታቸው፡፡ እግዚአብሔር ኢየሱስን ጌታም፣ ክርስቶስም አደረገው በማለት የተናገረውን ሃሳብ ስትመለከቱ በኢየሱስ በጌታና በክርስቶስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው ብላችሁ ሳትጠይቁ አትቀሩም፡፡

ዮሐንስ በወንጌሉ፣ “ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ብታምኑ…” (ዮሐ.20፡31) ሲል፣ ጳውሎስ ምስክርነት በጀመረበት ጊዜ፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር” ይላል (የሐዋ.9፡22)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ፣ “ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል›› (1ዮሐ.5፡1) በማለት ያስተምራል፡፡  

 የጴጥሮስም ዋና መልእክቱ የሚያጠነጥነውም በዚህ ዙሪያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስን ሥጋ (ሰብዓዊ) ሆኖ እንዲመጣና ለሰው ልጆች ኃጢአት እንዲሞት እንዳደረገው፣ ከሞት እንዳስነሳው፣ በከፈለው ዋጋ  ምክንያት እግዚአብሔር ከፍ ከፍ እንዳደረገውና ከስምም ሁሉ በላይ የሆነ ስም እንደ ሰጠው ያሳያል፡፡

አይሁዶች ስለ ኢየሱስ የሚያስቡት በመንደራቸው የተወለደ፣ ያደገና ወንድሞችና እህቶች ያሉት ሰው ብቻ አድርገው ነው፡፡ ጴጥሮስ ይህ በመንደራቸው የተወለደውና ያደገው ኢየሱስ እርሱ ጌታና የሚጠብቁት መሲህ (ክርስቶስ) እንደ ሆነ ሰበከላቸው፡፡ በስብከቱም ሕይወታቸው የተነካው ሁሉ ወደ ሦስት ሺ የሚሆኑት በኢየሱስ በማመን ሕይወታቸውን ለክርስቶስ በማስረከብ ጌታና አዳኝ አድርገው ተቀበሉት፡፡ ዛሬም የስብከታችን ማዕከል የኢየሱስ ክርስቶስነትና ጌትነት መሆን አለበት፡፡ በመከራው በሞቱና በትንሣኤው ላይ የተመሠረተ ስብከት የሰውን ሕይወት ይለውጣል፣ ያቆማል፣ ያጸናል፡፡ ሐዋርያትም ይህንን እንዳደረጉ ቃሉ ይነግረናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 5፡42፣ “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ማስተማርና መስበክን አይተውም ነበር” ይላል፡፡ የጴጥሮስና የሐዋርያት ስብከት የተመሠረተው በተሰቀለው በኢየሱስ ላይ ስለነበረ፣ መልእክታቸው ሕይወት-ለዋጭ ነበር፡፡ እኛም ዛሬ አንድ ጥቅስ እንኳን ሳናነብ፣ የራሳችንን ጀብዱ ብቻ ተናግረን ከመድረክ ከመውረድ ተቆጥበን፣ የተሰቀለውን የጌታን አዳኝነትና ጌትነት ብቻ እንናገር፡፡ መልእክት የምንሰማም ሰዎች ጆሮአችንን ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት ለሚናገሩና ለቃሉ ቅድሚያ ለሚሰጡ ብቻ እንክፈት፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *