‹‹በአንድ ድንጊያ ሁለት ወፍ›› እንደሚሉት፣ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ሁለት ሦስት ሐሳቦችን በአንድ ጊዜ መግለጽ ይችላል፡፡ ስለዚህ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለትን ስንመለከት የሁለት ነገሮች ፍጻሜ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለወንጌሉ ሥራ ኃይል የሚሆን የተስፋ ፍጻሜ ሲሆን፣ ሁለተኛው ወንጌልን ባለመቀበላቸውና ባለመታዘዛቸው የሚመጣ የፍርድ ፍጻሜን ያመለክታል፡፡
በብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ የተነገሩ ትንቢቶች ለአይሁዶች ግራ የሚያጋቡ ነበሩ፡፡ ክርስቶስ ኃያል፣ ብርቱ፣ ፈራጅና ንጉሥ ሆኖ ይመጣል ብለው አንዳንድ ነቢያት ሲናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል የተናቀ፣ የተጠላ፣ ደካማና የሕማም ሰው እያሉ የሚያቀርቡትና የሚገልጹት ትንቢቶች አይሁዶችን ግራ ስላጋቧቸው፤ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሥጋ (ሰብዓዊ) ሆኖ ሲመጣ አልተቀበሉትም፡፡
እንዲሁም ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገሩትም ሀሳቦች ግራ የሚያጋቡ ናቸው፡፡ እስኪ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ጥቅሶችን አብረን እንመልከት፡፡ በብሉይ ኪዳን የእስራኤላውያንን ታሪክ ስንመለከት ብዙ የሚያሳዝን ታሪክ አላቸው፡፡ በ931 ዓ.ዓ ንጉሥ ሰሎሞን በእስራኤል ንጉሥ በነበረበት ጊዜ አንድ ሺ ሚስቶች (ሰባት መቶ ሚስቶች፣ ሦስት መቶ ቁባቶች) አግብቶ፣ የእነርሱን ጣዖት በማምለክ በሠራው ኃጢአት ምክንያት የእስራኤል መንግሥት ለሁለት እንደሚከፈል እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያቱ ተናገረ፡፡
“እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው፡- ይህን ሠርተሃልና፣ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም፡፡ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም፡፡” (1ኛ ነገሥት. 11፡9-13)
እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ከመክፈሉ በፊት ግን አስቀድሞ ንጉሥ ሰሎሞን ከኃጢአቱ እንዲመለስ ቢያስጠነቅቀውም፣ ከኃጢአቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡ ስለዚህ በእርሱ ዘመን ሳይሆን፣ በልጁ ዘመን መንግሥቱን ለሁለት እንደሚከፍለው በተናገረው መሠረት ለሁለት ተከፈለ፡፡
በዚህም መሠረት፣ የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ሁለት ነገዶችን፣ ይሁዳና ብንያምን፣ ይዞ ይሁዳ ብሎ ሲገዛ፣ ኢዮርብዓም ደግሞ አሥር ነገዶችን ገንጥሎ እስራኤል ብሎ መግዛትና ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ሮብዓም የንጉሥ ሰሎሞን ልጅ ሲሆን፣ ኢዮርብዓም ደግሞ የሰሎሞን አገልጋይ (ባሪያ) ሲሆን፣ ከእርሱ ጋር በመጣላቱ ወደ ግብጽ ሸሽቶ ይኖር ነበር፡፡ ሰሎሞን መሞቱን ሲሰማ ወደ አገሩ ተመልሶ፣ ሕዝቡን ሰብስቦ ወደ ሮብዓም በመምጣት ሰሎሞን ያከበደባቸውን ቀንበር እንዲያቀልላቸው ቢጠይቁትም፣ ጥያቄአቸውን ሊቀበል ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ የአባቱ አማካሪዎች የመከሩትን ትቶ የወጣት አማካሪዎቹን ምክር በመቀበል፣ አባቱ ካስጨነቃቸው በላይ እንደሚያስጨንቃቸው ነገራቸው፡፡ እንዲህ በማለት “አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፣ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፣ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” የሚለውን መልስ በሰጣቸው ጊዜ ሕዝቡ ወደየ ድንኳኖቻቸው በመመለስ ኢዮርብዓምን ንጉሥ አድርገው አነገሡት፡፡
ኢዮርብዓምም ከነገሠ በኋላ አንድ አድርጎ ለመግዛት እንዲያመቸው ሕዝቡን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የማይቀርበትን የማስተሰሪያውን፣ የፋሲካውንና የበዓለ ኀምሳውን በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው እንዳያከብሩና እንዳያስቡት በሰሜንና በደቡብ፣ ዳንና ቤቴል በተባሉ ስፍራዎች የወርቅ የጥጃ ጣዖት የሚያመልኩበትን ቤተ መቅደስ ሠርቶ እንዲያመልኩ አደረጋቸው በ(1ኛ ነገሥ.12፡25-33)፡፡ በእስራኤል ወደ 20/21 የሚደርሱ ነገሥታት ነግሰዋል፡፡ ሁሉም በኢዮርብዓም መንገድ እንደ ሄዱ ቃሉ ያረጋግጥልናል፡፡ “ብዙ ጊዜ ተዘልፎ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል” (ምሳ. 29፡1) እንደሚለው ቃሉ፣ እግዚአብሔር በሦስት ነቢያት ከተናገራቸው በኋላ ከኃጢአታቸው ባልተመለሱና ባልታዘዙ ጊዜ፣ ለአሦራውያን ምርኮ በ722 ዓ.ዓ ላይ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡
በዚህ ጊዜ የሰሜኑ መንግሥት በኃጢአቱ ሲቀጣ፣ የይሁዳ መንግሥት በሠራው ኃጢአት ንስሐ መግባት ሲገባው፣ እንዲያውም ራሳቸውን እያኩራሩ የሰሜኑን መንግሥት እየኮነኑ፣ እኛ እንደ እስራኤል (የሰሜኑ መንግሥት) ለጠላት አልፈን አንሰጥም ማለት ጀመሩ፡፡ ምክንያት ሲሰጡ እኛ ቤተ መቅደስ፣ ታቦት፣ ተስፋና ቃል ኪዳን ያለን ሕዝቦች ነን እያሉ በኃጢአታቸው እየባሱ መጡ፡፡ በይሁዳም እንደ ሰሜኑ በተከታታይ 20 ነገሥታት ነግሰዋል፡፡
ከእነዚህም አራቱ እግዚአብሔርን ይፈሩ ስለ ነበር ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር እንዲጠጋና እንዲያመልክ አድርገውታል፡፡ የተቀሩት ነገሥታት ግን ሕዝቡ በኃጢአት እንዲቀጥልና እንዲጨማለቅ ዕድል ከፈቱለት፡፡ በተለይም ንጉሥ ምናሴ በነገሠበት ጊዜ የሚገዛውን ሕዝብ ደም አፍሳሽ፣ ጣዖት አምላኪና ልጁን ለሞራ ገላጮች መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ ኃጢአትን እንደ ውኃ የጠጣ ንጉሥ ነበር፡፡ (1ኛነገ.21፡10-15፤ 23፡26-27) ቢሆንም ግን እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ ስለሆነ ይሁዳን ከመቅጣቱ በፊት ወደ አምስት የሚደርሱ ነብያትን በየተራ አስነስቶ ወደ እግዚአብሔር ፍርድ እንዳይገቡ ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ አስጠንቅቆአቸዋል፡፡ እነርሱ ግን እግዚአብሔርን አልሰሙትም፣ ከኃጢአታቸውም አልተመለሱም፣ አልታዘዙም፡፡ ከእነዚህም ነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስ ነበር፡፡ ፍርድ መጥቶ ወደ ምርኮ ከመሄዳቸው በፊት፣ አስቀድሞ በጌታ ተልከው በተመሳሳይ ዘመን የተናገሯቸው ነቢዩ ኢሳይያስና ሚክያስ ናቸው፡፡ ኢሳይያስ ካስተላለፈው መልእክት አንዱ በኢሳይያስ 28፡9-13 ይገኛል፡፡ በተነገረው ትንቢት መሠረት ባለመታዘዛቸው ምክንያት በባቢሎናውያን ተማረኩ፡፡
“እንግዲያማ እግዚአብሔር፣ በባዕድ ልሳን በእንግዳ ቋንቋ ለዚህ ሕዝብ ይናገራል እርሱም “ይህቺ የዕረፍት ቦታ ናት የደከመው ይረፍ ይህቺ የዕረፍት ቦታ ናት” ያለው ለማን ነበር? እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፡፡ (ኢሳ.28፡11-12 አ.መ.ት) የትንቢቱ ሐሳብ ተፈጻሚነትን ያገኘው የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር ተማርከው ባሉበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሁለት ምርኮኛ ነቢያትን ዳንኤልንና ሕዝቅኤልን አስነስቶ በባቢሎናውያን (በባዕድ) ቋንቋ እንዲናገሯቸው አደረገ፡፡ ዳንኤል በ606 ዓ.ዓ ሕዝቅኤል በ597 ዓ.ዓ ላይ ከይሁዳ ተማርከው ወደ ባቢሎን የተወሰዱ ነበሩ፤ እግዚአብሔር እነዚህን ሁለት ምርኮኞች በምርኮ ለነበረው ሕዝብ ነቢያት አድርጎ አስነሳቸው፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን መልእክት ለሕዝቡ የንግድ ቋንቋ (ተራው ሕዝብ የሚግባባበት) በነበረው በባቢሎናውያን ቋንቋ መልእክታቸውን አስተላለፉ፣ ቢሆንም ግን የተላለፈውን የእግዚአብሔርን መልእክት ሕዝቡ አልሰሙትም፣ አልተቀበሉትም፣ አልታዘዙትም፡፡
0 Comments