ምዕራፍ አንድ ታላቁ ተልዕኮ የሚለውን ጨርሰን፣ ወደ ምዕራፍ ሁለት ታላቁ ተልዕኮ በኢየሩሳሌም ወደሚለው ርዕስ መግባት ጀምረናል፡፡ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡14-36ን ስንመለከት ጴጥሮስ በበዓለ-ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ከተሞላ በኋላ፣ ለበዓሉ ለተሰበሰቡት ሕዝቦች፣ ሕይወት-ለዋጭ የሆነውን ስብከት እንደ ሰበከ እናገኛለን፡፡ የሰውን ሕይወት ሊለውጥ የሚችል ስብከት መያዣና መጨበጫ የሌለው ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራዕይ ደርሶ የሚጨርስ ሳይሆን፤ መግቢያ፣ ሐተታና መደምደሚያ ያለው፣ በአንድ ሥፍራ ተወስኖ አውዱን ጠብቆ የሚቀርብ ነው፡፡ ከጴጥሮስም ስብከት እነዚህን እውነቶች በሚገባ በማየት እንችላለን፡፡

በዚህ ዘመን ከሚሰሙት ስብከቶች አንድ ሁለቱን ብቻ ላንሳ፤ አንድ ጊዜ ጓደኛዬ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ፣ አንድ የሰማውን ስብከት ነገረኝ፡፡ ስብከቱ የተመሠረተው በ1ኛ ዮሐንስ 2፡12-14 ባለው ክፍል ነበረ፡፡ ሰባኪው ሲሰብክ “ልጆቼ  ቼ ፈረሴ  እኛ አህያ አይደለንም  ፈረስ ነን” እያለ ሲሰብክ፣ ሰው ሁሉ “  እልል … ሃሌሉያ …” ይላል ብሎ ነገረኝ፡፡ እኔ ራሴ ደግሞ በአንድ ትልቅ ጉባዔ ላይ አንድ ሰባኪ ሲሰብክ ከሰማኋቸው አንዱን ብቻ  ላካፍላችሁ፡፡ ሰባኪው በመደጋገም “ክርስቶስ ወንድ ነው፤ ሰይጣን ሴት ነው” የሚል ነበር፡፡ የሴቶችን እኩልነት በሚያራምዱ መካከል ቢሆን፣ ሴቶች ይከሱት ነበር፤ ይህ የሴቶችን የእኩልነት መብት የሚነካ በመሆኑ፡፡ ከዚህም በላይ፣ እንዲህ ዓይነት ስብከት ወንድና ሴትን እኩል አድርጎ የሠራውን አምላክ ቅር ማሰኘት አይመስላችሁም?

እስቲ እናንተም እስከ ዛሬ የሰማችኋቸውን ፈር-የለቀቁ ስብከቶችን አስታውሱ፡፡ ከአውዱ የወጣ ስብከት ስትሰሙ ምን ተሰማችሁ? ፈር-የለቀቀ  መልእክት እንደፈለግን የምንሰብክስ ምን ይሰማናል? ለመሆኑ እኛ ሰባኪዎች በቃሉ ላይ ያልተመሠረተ ስብከት መስበክ አለመስበካችንን እንዴት እናውቃለን? ለነገሩ አንዳንዶቻችን ከአውዱ መውጣታችንን ስለማናውቀው፣ ምንም ላይሰማን ይችላል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም አቅም ስላጡ ዝም ማለትን መርጠዋል፣ ማንንም መናገርና ማረም አይፈልጉም፡፡ እኛም አገልጋዮች ማንም እንዲናገረንና እንዲያርመን አንፈልግም፡፡ በእኛ ላይ ማንም ሥልጣን የለውም ብለን ለራሳችን ነጻነትን ያወጅን እንመስላል፡፡

አንድ ጊዜ ከአንድ ወንድም ጋር አብረን እያገለገልን እያለ ከአውዱ በጣም ወጣ ያለ ስብከት ሰበከ፡፡ እኔም ይሰማኛል ብዬ ስላሰብኩኝ ምሳ እየበላን፣ ‹‹መልእክትህ ጥሩ ነበር” ብዬ ጥሩውን ጎኑን ከነገርኩት በኋላ፣ ‹‹እዚህ ቦታ ዐውዱን ጠብቀህ ብታቀርበው የበለጠ የሰዎችን ሕይወት ሊነካና እውነቱን እንዲይዙ ሊረዳቸው ይችላልና፣ ለወደፊቱ ብታስተካክለው›› ብዬ ስነግረው፣ ላለመቀበል የሰጠኝ ምክንያት “እኔ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበልኩት ስለሆነ ምንም ችግር አያመጣም፣›› በማለት  ሊቀበለኝ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ እኔም መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን መረዳት ከቃሉ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ጥንቃቄ ልናደርግ እንደሚገባን ነግሬው አገልግሎታችንን ጨርሰን ተለያየን፡፡  የጴጥሮስን ስብከት ስንመለከት የተሟሏ እንደ ነበረ እናያለን፡፡ የተሟሏ ስብከት የሚይዛቸውን ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ጴጥሮስ ድምጹን ከፍ አድርጎ በመግቢያው መናገር የጀመረው፣ “በኢየሩሳሌም የምትኖሩ አይሁድ” በማለት መልዕክቱ ለማን እንደሆነ፣ ሐዋርያትም ሰክረው እንዳልሆነና በነብዩ ኢዩኤል የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ ማግኘቱን ካሳያቸው በኋላ፣ ወደ ዋናው ሐሳብ በመግባት መልዕክቱን አስተላለፈ፡፡ በመልዕክቱም ውሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ወደ እነርሱ የተላከ አዳኝ ቢሆንም፣ እነርሱ ሰቅለው እንደ ገደሉት መሳሳታቸውን አሳያቸው፡፡ በዳዊት ትንቢት መሠረትም በሦስተኛው ቀን ከሞት እንዳስነሳውና በቀኙ እንዳስቀመጠው፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ እንዳፈሰሰላቸው ነገራቸው፡፡ በመጨረሻም በቁጥር 36 ላይ ‹‹እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይወቅ ›› ብሎ በመናገር ደመደመ እንጂ፣  የመንፈስ ቅዱስ ልምምዱን፣ ተስፋውን እንዴት እንደጠበቀ፣ እንዴት  እንዳገኘው አልሰበከም፤ ይልቁንም ዋናውን ቁም ነገር የሰውን ሕይወት ሊለውጥ የሚችለውን ጌታ ነበር ያሳያቸው፡፡ እኛም በስብከታችንና በአገልግሎታችን የዓለም አዳኝ የሆነውን ጌታን ብቻ እናሳያቸው፡፡ እርሱ ሲሰበክ ሕይወት ይለወጣል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *