ለመሆኑ የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ በብሉይ ኪዳን ተነግሮ ነበር? እስቲ የተወሰኑ በብሉይ ኪዳን የተነገሩ ትንቢቶችን እንመልከት፡፡ ኢዩኤል ከ800 ዓመት በፊት፣ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ አፈሳለሁ” (2፡28) ሲል፣ ሕዝቅኤል ደግሞ፣ “…አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ … መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ … ” (36፡26-27) በማለት እግዚአብሔር ወደፊት በልጁ በኩል መንፈስ ቅዱስን ለሚያምኑበት ሁሉ እንደሚሰጥ በትንቢታቸው ያመለክታሉ፡፡ ኢሳይያስም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚጀምር በሚከተለው መንገድ በመግለጽ ስለ መንፈስ ቅዱስ በጌታ ላይ ስለ ማረፉ፣ መሰጠቱና አገልግሎቱ ይናገራል፡፡ “የእግዚአብሔር መንፈስ የጥበብና ማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል፡፡” ይላል፡፡ (ኢሳ.11፡1-2) ጌታ በተጠመቀበት ቀን ትንቢቱ ፍጻሜ ሲያገኝ፣ በቀጣይነቱ በሚያምኑት ልጆቹ ላይ፣ ጌታ ለገባው ቃል ታማኝ ስለሆነ በጊዜውና በሰዓቱ መንፈስ ቅዱስን በበዓለ ኀምሳ ቀን ሰጣቸው፡፡

  ዛሬስ እኛ የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ተቀብለናል?  ብዙ ግራ  የሚያጋቡ ነገሮች ገጥመውን ሊሆን ይችላል፡፡ በእሳት ተጠመቅ፣ በልሳን ተናገር፣ ጹምና ጸልይ፣ በትዕግሥት ጠብቅ፣ አንዳንዶች እንዳደረጉትም ሰውነትህን በእሾህ ግረፍ … እነዚህን የመሳሰሉትን ሁሉ አድርጋችሁ ግራ ተጋብታችሁ ይሆን? በእኔም ሕይወት ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አልፈዋል፣ ቢሆንም ግን ጌታ ቸርና ሩኅሩህ ስለሆነ ግራ ስጋባ ዝም ብሎ አልተመለከተኝም፡፡

 አንድ ጊዜ አንድ አገልጋይ በጸሎት ቤት ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት እየተጸለየልኝ አለመሞላቴን ስለ አየ፣ በጣምም ይወደኝ ስለ ነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት በግሉ ሊጸልይልኝ ፈልጎ “እቤቴ መጥተህ እያደርክ እንጸልያለን” ብሎኝ እቤቱ እየሄድኩኝ በማደር እንጸልይ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቤቱ አድሬ ጸሎት ተጀመረና በምንጸልይበት ጊዜ እጁን በዓይኔ ላይ አድርጎ ሲጸልይ፣ እስኪፈርጥ ድረስ በኃይል ስለተጫናቸው ዓይኔ ከሚፈርጥ ብዬ ‹‹ሃሌሉያ ሃሌሉያ …›› በማለት (በዘመኑ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የሚባል የመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ጌታ ያስተማረው ሳይሆን የሰው ፎርሙላ ነበር) ቶሎ እንዲለቀኝ አድርጌአለሁ፡፡ ይህ ኳስ የሚያክለው ዓይኔ እንኳን ተጭነውት ራሱ ወደ ውጭ ሊወጣ የደረሰ አደጋ የማይችል ነው፡፡           

ሐዋርያት በተለያየ ነገር ራሳቸውን አላስጨነቁም፡፡ ጠብቁ በተባሉት መሠረት በጸሎት እየተጉ ሲጠብቁ ሳሉ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በድንገት ወረደላቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ጊዜ ኃይሉን ተቀበሉ፡፡ ከዚያ በፊት ፈሪዎችና በኃጢአት ላይ አሸናፊነት የሌላቸው ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በቤት ሠራተኛ ፊት የካዱት ሳይቀሩ ሁሉም በድፍረት ስለ ጌታ መመስከር ጀመሩ፡፡ ወንጌልን በድፍረት በሰዎችና በመሪዎች ፊት ስለ አዳኝነቱና ጌትነቱ አወጁ፡፡ ጌታን ካገኘንበት ቀን ጀምሮ በሕይወታችን ለውጥ ያመጣው ማነው? ለውጥ ካለ፣ ያንን የሠራው ማነው? እኛ ሳንሆን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በኃጢአት ላይ ድልን የሰጠን፣ በቅድስና ሕይወት እንድንኖር የረዳን፣ የሚጠሉንን እንድንወድ የረዳን፣ ለውጥን በሕይወታችን ያመጣ፣ ሰላምን የሰጠን፣ ጌታ ከአባቱ ጋር ሲያስታርቀን መታረቅ የቻልነው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው፡፡ እነዚህ የዘረዘርኳቸው ነገሮች በሕይወታችን ከሌሉ ራሳችንን ልንጠይቅ ያስፈልጋል፣ ነቢያቱና ጌታ የተናገሩት በእኔ ሕይወት ተፈጽሞአል? በእውነት ተለውጫለሁ? መንፈስ ቅዱስ በውስጤ አለ?  ማደሪያው ሆኛለሁ? “… ከላይ ኃይል እስክትለብሱ… ቆዩ” የተባለለት ኃይሉ በእኔ ውስጥ አለ? በሐዋርያት ሕይወት የተፈጸመው በእኔ ሕይወት ተፈጽሞአል? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እኛ በጸሎት እየተጋን ስንጠብቅ፣ ጌታ አይዋሽምና የተስፋ ቃሉን በሕይወታችን  ይፈጽማል፡፡ ከእኛ ማንነት የተነሳ ሳይሆን፣ እርሱ በቃሉ ታማኝ ስለሆነ ያደርገዋል፡፡ ይህን ተስፋ ከተቀበልን፣ የተቀበልነውንና ሕይወታችንን የለወጠውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ለሰዎች ሁሉ ልንናገር ይገባናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *