ሐዋርያት ትኩረታቸውን በተልዕኮ ላይ እንዳላደረጉ ባለፈው ተመልክተናል፡፡ ለመሆኑ፣ ተልዕኮ ምንድን ነው?  እስከ አሁንም ተልዕኮ፣ ተልዕኮ ስንል ብዙ ቆይተናል፤ ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የተለያዩ የግል ድርጅቶች አሁን አሁን ላይ ስንመለከት ሁሉም ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች በማለት የማንነታቸው መገለጫዎችን ይጽፋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ተልዕኮ ነበረው፤ ተልዕኮውም የሰው ልጆችን ከአብ ጋር ለማስታረቅ በመስቀል ላይ ደሙን ለኃጢአታችን በማፍሰስ የሠራው ድነት ነው፡፡ ሐዋርያትም ኢየሱስ የፈጸመውን የድነት ሥራ ለሰዎች መንገርና ማወጅ እንዳለባቸው በማቴዎስ ምዕራፍ 28፡19-20 እንዲህ በማለት በሚገባ አስገንዝቧቸዋል፡- “… ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን(ሕዝቦችን) ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፡- ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡”

ጌታም ሐዋርያትን ለሦስት ዓመት ተኩል ያሰለጠናቸውም ለዚህ ዓላማ ነበር፡፡ ክብሩን ትቶ እንዲመጣ  ያደረገው በምድርም በነበረ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶት የነበረውም  ይህን ዋና ተልዕኮ ለመወጣት ነበር፡፡ ጌታም ሐዋርያት ትልቅ ትኩረት እንዲሰጡት የፈለገው በዚህ በዋናው ተልዕኮ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ቀደም ብለን እንዳየነው ተልዕኮው በሦስት ዋና  ዋና ነገሮች ላይ ያተኩራል፣ እነርሱም፡- (1) የመንፈስ ቅዱስ መውረድ፣ (2) ኃይል መቀበል፣ እና (3) ምሥክር መሆን ናቸው፡፡ የተልዕኮውንም ስፋት ሲገልጽ ከኢየሩሳሌም ተነስቶ እስከ ዓለም  ዳር እንደሚደርስም አመላክቶአቸዋል፡፡

 የሐዋርያት ሥራን ስንመለከት፣ በምዕራፍ አንድ ላይ እንደምናየው በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት እየተጉና በይሁዳ ቦታ የጎደለውን እየመረጡ ሳለ በድንገት የተገባላቸው የተስፋ ቃል ተፈጸመላቸው፡፡ ጌታ ከአብ የተቀበለውን የተስፋ ቃል በበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስን በመላክ በእርሱ በኩል የሚጠበቀውን እንደፈጸመላቸው በምዕራፍ 2 ላይ ማየት እንችላለን፡፡ ‹‹በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፣ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው፡፡ እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፣ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር፡፡ (የሐዋ.2፡1-4) በስደት ምክንያት በየቦታው ተበታትነው የነበሩ አይሁድ በዓለ ኀምሳን ለማክበር በተሰበሰቡበት ሥፍራ ሐዋርያት በማያውቁትና ባልተማሩት፣ በዚያ የተሰበሰበው ሕዝብ በሚሰማውና በሚያውቀው ቋንቋ/ልሳን እንዲናገሩ ማድረጉ አስደናቂ ተዓምር ነበር፡፡ ምክንያቱም ዮሐንስ በወንጌሉ እንደሚናገረው ጌታ ከተለያቸው በኋላ በፍርሃት ውስጥ ነበሩ (ዮሐ. 20፡19)፡፡ ስለዚህ ከዚህ ፍርሃት ገና ባልተላቀቁበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ ተፈጽሞ በመካከላቸው ማየታቸው ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራ ነበረ፡፡ ጌታ በቃሉ አይዋሽም፣ ታማኝ እንደሆነም አዩ፡፡ ዛሬም ብዙዎቻችን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ለመቀበል እንጨነቃለን፣ በጾም በጸሎት እንሆናለን፣ ቀንና ሰዓት ወስነን ለማግኘት እንጥራለን፡፡ ነገር ግን እኛ እንዳሰብነውና እንዳቀድነው ሳይሆን፣ ተስፋውን የሰጠው እርሱ ስለሆነ፣ በእርሱ ጊዜና ሰዓት ሳናስበው በድንገት፣ ሐዋርያትን እንዳጠመቃቸውና እንደሞላቸው እኛንም ያጠምቀናል፣ ይሞላናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን መስጠት የእርሱ ድርሻና ኃላፊነት ሲሆን የሐዋርያትም የእኛም ኃላፊነት ደግሞ ምሥክር ለመሆን ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጌታ ለሐዋርያት የሰጠው ዋናው ተልዕኮ ይህ ሲሆን፣ የእኛም ተልዕኮ ከዚህ የተለየ ሳይሆን ይህን  ክርስቶስ  በመስቀል ላይ የፈጸመውን የጽድቅ ሥራ፣ ሰዎች አምነው እንዲድኑበትና ከአምላካቸው ጋር እንዲታረቁበት የምሥራቹን  ለሰዎች ማብሰር ነው፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *