ባለፈው ተለቆ ባየነው ጽሑፍ ሐዋርያት ጌታ ካረገ በኋላ፣ በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት መሰብሰባቸውን አንብበናል፡፡ እግዚአብሔር ሥራው እንዲሠራ ከሁሉ በላይ አንድ ልብ ይፈልጋል፡፡ የሐዋርያት ሥራ 1፡14፤ 2፡1፣46፤ 4፡26፣32፤ 5፡12  በእነዚህ ሁሉ ጥቅሶች ስንመለከት በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጌታ የቀረቡበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ለማግኘት አንድ ልብ መሆን እንደ ጠቀማቸው እናያለን፡፡ ለመሆኑ በአንድ ልብ መሆን እንዴት ቻሉ? የተለያየ ሀሳብ የላቸውም ማለት ነው? አይደለም፡፡ የተለያየ ሀሳብ ቢኖራቸውም፣ ጌታ ባዘዛቸው መሠረት ሁሉም በአንድ ላይ በመስማማት የተባሉትን ለመፈጸም ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው ሲጠብቁ እናያለን፡፡

 ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስን አማኞች በአንድ ልብ እንዲሆኑለት፣ “በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፣ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፣ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፣ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ ደስታዬን ፈጽሙልኝ …” በማለት ይለምናቸዋል፡፡ (ፊልጵ 2፡1-2) ጳውሎስ መልዕክቱን በሚጽፍበት ጊዜ ምንም እንኳን በእስር ቤት ቢሆንም በታላቅ ደስታ ውስጥ ነበረ፡፡ ከተደሰተባቸው ምክንያቶቹ ሁሉ በሁለቱ እጅግ ደስ ብሎታል፡፡ የመጀመሪያው ጌታን በማግኘቱ ያገኘው ሲሆን፣ ሁለተኛው የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች መታሠሩን ሰምተው ገንዘብ አዋጥተው ስለላኩለት ነበር፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥት የሆነ አንድ ድርጊት አስታወሰኝ፡፡ በ1971 ዓ.ም በእምነቴ ምክንያት እስር ላይ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ቀን ጠዋት አንዲት የእሁድ ትምህርት ቤት ተማሪ ልትጠይቀኝ ስትመጣ ትንሽ ቂጣ ይዛልኝ መጣች፡፡ ይህች ልጅ ይዛልኝ የምትመጣው ምንም ነገር አልነበራትም፣ ነገር ግን ለቁርስ የተሰጣትን ይዛ መምጣቷ ምን ያህል ከጌታ ባገኘችው ፍቅር እንደምትወደኝ ፍቅሯን የምትገልጽበት መንገድ ነበረ፡፡ ይህ ድርጊቷና ጦሟን መዋሏ እስከ አሁን ድረስ ለ40 ዓመት ያህል እንደ ሥዕል እየታየኝ ከፊቴ አልጠፋም፡፡  

ጳውሎስም ገንዘብ አዋጥተው ስለ ላኩለት እጅግ በጣም ደስ ብሎታል፡፡ አሁን ግን ደብዳቤውን ሲጽፍላቸው ደስታውን ከሚያጠፉበት ነገሮች አንዱን ስለ ተመለከተ፣ ደስታዬን ፈጽሙልኝ ይላቸዋል፡፡ ይህም ከእርሱ ጋር አብረው በወንጌል ያገለገሉና የተጋደሉ፣ በወገናዊነት፣ በከንቱ ውዳሴ (ራስን በመውደድ)፣ ሌላውን ዝቅ አድርጎ በማየት ምክንያት በቤተ ክርስቲያን አንድ ልብ እንዳይኖር ያደረጉ፣ ኤዎድያንና ሲንጤኪን የተባሉ  ሁለት እህቶችን ይጠቅሳል፡፡ ዛሬም ቢሆን በዚህ ዘመን የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት አንድ ልብ መሆን እጅግ ጠቃሚና ጌታን የሚያስደስትና ፍሬያማ የሚያደርግ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በየዘመናቱ አንድ ልብ እንዲኖረንና በመስማማት አብረን እንድናገለግል የመውቀስ ሥራውን አላቆመም፡፡ በዚህም መሠረት የተስፋው ቃል ተፈጽሞ ጌታ በመካከላችን እንዲሠራና በአንድ ልብ ለመሆን እንድንችል በመጀመሪያ የሚቀባበል ልብ፣ ከዚያም ይቅር የሚል ልብ ሊኖረን ይገባል፡፡ ከሌሎች ጋር አንድ ልብ እንዲኖረን “እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና” (ማቴ. 11፡29) ያለው የጌታ ልብ ሊኖርን ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ ወደፊት ለማስኬድና አንድ ልብ እንዲኖረን እንደ ሐዋርያት ወደ ጌታ በብርቱ መጸለይና ራሳችንን ማዋረድ ይገባናል፡፡ ለዚህም ጥረታችንና ለምንወስደው እርምጃችን ጌታ ይርዳን፣ ጸጋውን ያብዛልን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *