ተስፋ የማናየው የማንጨብጠው ወደፊት የሚጠበቅና የሚፈጸም ነው፡፡ ተስፋ ባይኖር የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ መኖር አይችልም ነበር፡፡ የታመመ እድናለሁ፣ የከሰረ አተርፋለሁ፣ ሥራ ያጣ አገኛለሁ፣ ፈተና የወደቀ አልፋለሁ ብሎ ተስፋ ባይኖረው ኖሮ፣ የሰው ልጅ የዚህን ዓለም ችግርና ፈተና ተቋቁሞ አሁን የደረሰበት ባልረሰ ነበር፡፡ ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው በውስጡ ያስቀመጠለት ስጦታው ነው፡፡ ይህን ተስፋ ሲያጣ ነው ሰው ራሱን ወደ ተለየዩ ሱሶች ውስጥ የሚያስገባው፤ መጠጣት፣ ጫት መቃም፣ ሲጋራና ሀሺሽ ማጨስ፣ የመሳሰሉትን ካደረገ በኋላ ምንም ተስፋ ስለማያገኝ ራሱን ወደ መስቀል፣ መርዝ ወደ መጠጣት፣ በመሣሪያ ራስን ወደ ማጥፋት የሚመጣው ተስፋን ከማጣት የተነሳ ነው፡፡
ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ ሲለያቸው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይገቡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፡1 ላይ ‹‹ልባችሁ አይታወክ፣ በእግዚአብሔር እመኑ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡›› ብሎ ተስፋ እንዳይቆርጡ አስቀድሞ ማጽናናት ጀምሮ ነበር፡፡ በመቀጠልም እንደሚለያቸው እርግጠኛ በሆነበት ሰዓት ላይ፣ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይገቡ ሊሆን ያለውን ነገር ሁሉ በማስረዳት ከአባቱ በእርሱ በኩል የተገባላቸውን የተስፋ ቃል እንዲጠብቁ እንደነገራቸው ሉቃስ ዘግቦልናል፡፡ ስለዚህ በቁጥር 4 እና 5 ላይ ያሉትን ሐሳቦች ስንመለከት፣ ጌታ ኢየሱስ በምድር አብሮአቸው በነበረ ጊዜ የሦስት ዓመት ተኩሉን ሥልጠና ጨርሶ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ከመሆኑ በፊት ሦስት ዋና ዋና ነገሮችን እንደ ነገራቸው ሉቃስ በወንጌሉ በምዕራፍ 24፡49 ላይ ዘግቦት እናገኛለን፡፡ ሐዋርያትም የታዘዙት፡- (1) ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ፤ (2) አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል እንዲጠብቁ፣ እና (3) በመንፈስ ቅዱስ እንዲጠመቁ ነበር፡፡ የሐዋርያትን ታሪክ ስንመለከት፣ በደብረዘይት ተራራ ላይ ዕርገቱን ከተመለከቱና ወደ ላይ አሻቅበው እያዩት ከሸኙት በኋላ፣ ተስፋ ቆርጠው ወደ ተለያየ ሥራቸውና ተግባራቸው አልተበታተኑም፡፡ እንደ ታዘዙት በአንድ ዓላማ ሆነው ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም በመውጣት በሚኖሩበት ሰገነት ላይ በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት መትጋት ጀመሩ፡፡ መቶ ሀያ የሚሆኑ አማኞች አንድ ላይ ሆነው በጸሎት እየተጉና የተስፋውን ቃል እየጠበቁ ሳሉ፣ ምንም ጊዜው ረዝሞ ዐርባ ቀን ቢጠብቁ፣ ከመካከላቸው በጎደለው በይሁዳ ቦታ ሰው መርጠው ሳለ፣ ተገብቶላቸው የነበረው የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ ድንገት ሳያስቡት እንደ ወረደላቸውና በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞሉ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ታሪክ ይነግረናል፡፡
0 Comments