ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ሕያው ሆኖ በመነሳት ለዐርባ ቀን ራሱን አሳያቸው፡፡ በዚህ ዐርባ ቀን ውስጥ ወደ አሥራ አንድ ጊዜ ራሱን ሲገልጥ የታየው ለአማኞች ብቻ ነበረ፡፡ ለመግደላዊት ማርያም፣ ለእነ ጴጥሮስ፣ ለኤማሆስ መንገደኞች፣ ለአሥራ አንዱና ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በተለያየ ጊዜና ለሌሎችም … መታየቱን ከሚከተሉት ጥቅሶች መረዳት እንችላለን፡፡ ‹‹…ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ…››፣ ‹‹… እንደተናገረ ተነስቶአልና…››፣ ‹‹… ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ፡፡››፣ ‹‹… ሥጋውንም ባጡ ጊዜ … ጌታ በእውነት ተነስቶአል…›› (ዮሐ.20፣ ማቴ.28፣ ማር.16፣ ሉቃ.24) የሚሉት ሐረጐች የክርስቶስን ሕያውነት ያመለክታሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራም መጽሐፍ ይህንኑ ጌታ ሕያው ሆኖ በማየታቸው በእምነታቸው ጠንክረውና በርትተው ያዩትን ለሌሎች ለመናገር ራሳቸውን በሚገባ ማዘጋጀታቸውን ያሳየናል፡፡ እኛም የሐዋርያትን ታሪክ ብቻ ተርከን ማለፍ ሳይሆን፣ ከብርታታቸውና ከድካማቸው ለራሳችን ትምህርትን ወስደን እንድንለወጥበት ያስፈልገናል፡፡
ዛሬም የክርስቶስን ሕያውነት ማየት የሚችሉት የተጠሙ የተራቡና ተዘጋጅተው ራሳቸውን ለጌታ አሳልፈው የሚሰጡ ብቻ ናቸው፡፡ ሕይወት የመረራቸው፣ በዚህ ዓለም መኖር ያስጠላቸው፣ በመጠጥ፣ በተለያዩ ሱሶች የተቸገሩ፣ በጥንቆላ ሥራ ገንዘባቸውን የጨረሱ፣ ትዳራቸው የፈረሰ … በማቴዎስ ምዕራፍ 11፡28 ላይ ያለውን “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡” የሚለውን ጥሪ የሰሙ ሁሉ ወደ እርሱ ሲመጡ ሕይወታቸው ተለውጦ፣ አሮጌው ነገር ሁሉ አልፎ፣ አዲስ ፍጥረት ይሆናሉ፡፡ ለዚህ የሕይወት ለውጥ ያገኘን ሁላችን ምስክሮች ነን፡፡
ያ ሰካራም፣ ውሸታም፣ ዝሙተኛና ሱሰኛ ሕይወታችን የተለወጠው፣ ክርስቶስ ዛሬም ሕያው ሆኖ በመካከላችን በመመላለሱና የሰውን ሕይወት መለወጥ በመቻሉ ነው፡፡ ዛሬ በአንተ/በአንቺ ሕይወት ክርስቶስ ሕያው ካልሆነና ከእነዚህ ነገሮች ካልተላቀቃችሁ ራሳችሁን ልትጠይቁ ይገባል፡፡ ቃሉ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትላንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው” (ዕብ. 13፡8) ስለሚል፣ ክርስቶስ ከ2000 ዓመት በኋላም ሕያው ስለሆነ፣ ዛሬም የሰውን ሕይወት ይለውጣል፣ ኃይሉ አልተለወጠም፡፡ ብዙ ጊዜ በሕይወታችን ለውጥ የማይመጣው ችግሩ እኛ ጋ ስለ ሆነ ነው፤ ወደ ጌታ ቀርቦ ሕይወትን ለእርሱ መስጠት፣ ማስረከብና በእርሱ መደገፍ ይፈለግብናል፡፡ በሕይወት የደከምንም ካለን ችግሩ የት ጋ እንደሆነ ለይቶ ማወቅና በንስሐ መታደሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ክርስቶስ በእኔ ሕይወት ሕያው ስለሆነ ከእነዚህም በላይ አልፎ የአጎቴን ውቃቢ ከመካደም፣ ሰውን ለማሳበድና ለመገደል ካጠናሁት የመጽሐፍ መግለጥ ጥንቆላ ነፃ አውጥቶ አገልጋይ አድርጎኛል፡፡ ዛሬ ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ችያለሁ፡፡ ይህ ለክርስቶስ ሕያውነት አንድ ምስክር ነው፡፡ በእኔ ሕይወት የሠራው ጌታ ዛሬም በሌሎችም ሕይወት እየሠራ እንደሆነ ከተለያዩ ክርስቲያናዊ ቻናሎች ማየትና መረዳት እንችላለን፡፡ በሕይወታችን የሠራው ጌታ ስሙ የተባረከ ይሁን፡፡
0 Comments