ሉቃስ የጳውሎስን ታሪክ በስፋት የጻፈው ለምንድነው? የሚለውን ቀደም ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ ሉቃስ ስለ አህዛብ መለወጥ ከመጻፉ በፊት ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ተስፋውን የመጠበቅ ትዕዛዙን እንደ መግቢያ ተጠቅሞበታል፡፡ የመልእክቱ የመጀመሪያ ዓላማ  ሕያው የሆነው ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በመቀጠል ያደረገውንና የሠራውን ለወዳጁ መግለጽ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ ጸሐፊው ትልቅ ትኩረት የሰጠው ስለ አሕዛብ (ከአይሁድ ውጭ ያሉ ሕዝቦች) መዳን ነው፣ ምክንያቱም የጳውሎስ አገልግሎት የተያያዘውና የተቆራኘው ከአሕዛብ ጋር በመሆኑ ነው፡፡ ስለ አሕዛብ ወንጌልን መቀበልና መዳን ወደፊት በስፋት እንመለከታለን፡፡ ለሉቃስ ጽሑፍ ምክንያት የሆነው ከጳውሎስ ጋር አብሮ ማገልገሉ እንደሆነ ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ፣ በተለይም እስከ ምዕራፍ 15 ድረስ፣ ስለ ራሱም ሆነ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ስለመሆኑ የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ከምዕራፍ 16፡10 ላይ ስንደርስ ግን፣  “እኛ”  እያለ የሚናገረውና ‹‹ወረዱ›› የሚለው  ቃል ወደ ‹‹ልንወጣ ፈለግን››  በሚሉት ቃሎች መለወጣቸው ሉቃስ ከጳውሎስ ጋር አብሮ መሆኑን ያሳዩናል፡፡ ሉቃስ ስለ መለወጡ ሳይነግረን፣ ስለ አገልግሎቱ ሁኔታ ይገልጻል፡፡   

የሐዋርያት ሥራን ከምዕራፍ 1፡1-5 ያለውን መግቢያውን ስንመለከት፣ የሉቃስ ወንጌልንና የሐዋርያት ሥራን የሚያገናኘውን ሐሳብና ምንጫቸው አንድ መሆኑን እናገኛለን፡፡ “ቴዎፍሎስ ሆይ፡- ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፡- ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤(በወንጌሉ) ደግሞ ዐርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፡- በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው፡፡ ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፣ ነገር ግን፡- ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ፡፡” (የሐዋ.1፡1-5) በመንፈስ ቅዱስ አዘዛቸው፣ ያደርገውና ያስተምራቸው፣ ዐርባ ቀን፣ ሕያው ሆኖ  የሚሉት ሐሳቦች ትኩረት የሚሠጣቸው ናቸው፡፡ ሉቃስ ለቴዎፍሎስ ሲጽፍለት ሐዋርያትን ጌታ በመንፈስ ቅዱስ እንዳዘዛቸው ‹‹ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ›› ስላለው ነገር እንደ ጻፈለት በማስታወስ፣ የሚቀጥለውን ታሪክ ይቀጥልለታል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር በመምጣት እንደ እግዚአብሔር አምላክ፣ እንደ ሰው ሰው ሆኖ ሁለቱን በማስታረቅ የድነትን ሥራ እንደሠራ ገልጾለታል፡፡ (1.ጢሞ.2፡5) የሉቃስ ወንጌልን የጻፈበትን ምክንያት ከገለጸለት በኋላ፣ አሁን ደግም ቀጣይ የሆነውን የሐዋርያትን ሥራ የጻፈበትን ምክንያት ይናገራል፡፡ “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፣ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው” ቁ.3፡፡ ጌታ ጠብቁ ብሎ በመንፈስ ቅዱስ ባዘዛቸው የተልዕኮው ትዕዛዝ መሠረት ሕያው ሆኖ ራሱን አሳያቸው፡፡ ስለ ጌታ ሕያውነት በሚቀጥለው በሚለቀቀው ጽሑፍ ይጠብቁ፡፡    


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *