ባለፈው የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ በሚለው ርዕስ ሥር የተወሰነ ጥቂት ሀሳብ አይተናል፡፡ እግዚአብሔር አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን የማዳን ዕቅድ ሲያወጡ በህብረት ሥራ ተከፋፍለው እንደሆነ በቃሉ ማየት እንችላለን፡፡ በዕቅዳቸው መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማርያም ማህፀን አድሮ ሰው ሆኖ ተወልዶ፣ አድጐ በምድር ላይ እንደማንኛውም  ሰው ሆኖ በመመላለስ፣ ቤተ ሰቡንም በማገልገል ለሠላሳ ዓመት ቆየ፡፡ በመቀጠልም የመጣበትን የአባቱን ተልዕኮ ለመፈጸም አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርትን መርጦ ለሦስት ዓመት ተኩል ሲያሰለጥናቸው ቆይቶ፣ ወደ አባቱ ከመሄዱ በፊት ተልዕኮውን ለደቀመዛሙርት አሳልፎ በመስጠት የመጨረሻ ስንብቱን አደረገ፡፡

 ሐዋርያትም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተልዕኮውን ተቀብለው ይዘው ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ እንመለከታለን፡፡ ወንጌላዊ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 1፡8-9 ላይ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል ‹‹… መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም፣ እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› አለ፡፡ ‹‹ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው››፡፡   ‹‹በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፣ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው፡፡›› ቁ 12. በዚያም በጸሎት መትጋት ጀመሩ፡፡ ሥላሴ በህብረት እንደ ሠሩ ደቀ መዛሙርትም በህብረት እንዲሠሩት ተልዕኮ ተሰጣቸው፡፡ ይህ ተልዕኮ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ በህብረቱ ውስጥ ስላለን የተልዕኮው ተካፋዮች ሆነናል፡፡ ተልዕኮው ለደቀ መዛሙርት ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ለአማኞች ሁሉ የተሰጠ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ተልዕኮውን በግል መወጣት እንችላለን፣ ነገር ግን በህብረት ብንሠራው የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፡፡  በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት ሐዋርያት ወንጌሉን ይዘው በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከየት ወዴት እንዳደረሱት እንመለከታለን፡፡ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል የወሰደችውን ርምጃ በማየት ወደ ዘመናችን እናመራለን፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በስፋት የምንመለከተው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን በሙሉና በዝርዝር ሳይሆን ትኩረታችን የሚሆነው በኢየሩሳሌምና በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ይሆናል፡፡ ሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት ተልዕኮውን ተቀብለው እንዴት እንደተወጡት በማወዳደር እንመለከታለን፡፡ ተልዕኮውን በህብረት ለመወጣት የትኛዋ ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ ጥረት ስታደርግ እናያታለን? ችግር ገጥሟቸውም ከሆነ እንዴት ተወጡት?


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *