ሰዎች በዚህ ምድር ስንኖር የተለያየ ተልዕኮ ይኖረናል ፡፡ በመጀመሪያ ተልዕኮ ማለት ምን ማለት ነው? ብለን ስንጠይቅ የተለያዩ ሀሳቦች እናገኛለን፡፡ ተልዕኮ በእንግሊዝኛው (mission) ብለን የምንጠራው ነው፡፡ መሪዎች፣ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ሁሉም የየራሳቸውን ተልዕኮ በወረቀትና በሚታይ ቦታ ጽፈውት ይታያል፡፡ ሁሉም ተልዕኮአቸውን ለመወጣት የተለያየ ጥረትም ያደርጋሉ፡፡
በዘፍጥረት መጽሐፍ ስንመለከት እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ የደህንነት መልዕክት ለዓለም እንዲያስተላልፉ ተልዕኮ ሰጣቸው፡፡ ሰው በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ሕይወት ተለይቶ በሰይጣን እጅ ወድቆ ስለነበረ ተልዕኮው አስፈላጊ ነበረ፡፡ (ዘፍ.3፡24፣ ሮሜ 1፡21-25.) እግዚአብሔር የደህንነት መንገድ ቢያዘጋጅም፣ የዓለም ሕዝብ ደህንነትን እንዲቀበል፣ የእግዚአብሔር ሰዎች አስቀድመው ስለ ደህንነቱ መናገር ነበረባቸው፡፡(ሮሜ 10፡13-15፣ 2ቆሮ. 5፡18-19) መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሰዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማዳን ዕቅዱን እንዴት እያደገ እንደመጣ ይተርክልናል፡፡ የደህንነቱ በረከት ለዓለም ሕዝቦች በእስራኤል በኩል እንዲደርስና የአንድ ሕዝብ አባት እንዲሆን እግዚአብሔር አንድ ሰው (አብርሃምን) መረጠ፡፡ እስራኤል የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔርን እንዲያውቁና ወደ እርሱ እንዲጠጉ ለማድረግ የተመረጠች ወኪል ነበረች፡፡ (ዘፍ.12፡2-3፣ ዘፀ.19፡5-6) እስራኤል ግን በተለያየ ምክንያት የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ስለ አለፈች ተልዕኮውን ለዓለም ሕዝቦች ማድረስ አልቻለችም፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ከዚሁ ዘር ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ በማድረግ የዓለም አዳኝ አድረጐ ላከው፡፡ (ሉቃ.2፡10-11) ጌታም ይህን ተልዕኮ ይዘው ወደ ተለያዩ ሕዝቦች እንዲሄዱ አዲስ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን መሠረተ፡፡ (ማቴ. 28፡19-20፣ የሐዋ. 1፡8) ለመጀመሪያ ጊዜ ይህችን ቤተ ክርስቲያን በመምራት ተልዕኮውን እንዲወጡ የተመረጡት ሐዋርያት ተልዕኮውን ከየት ወዴት እንዳደረሱት በሚቀጥለው በምለቀው ጽሑፍ ማየት ይቻላል፡፡
0 Comments