የመጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊነት
6.1 የቃሉ አንድነት
ባለፈው ጥናታችን መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ተመለክተን ነበር፤ እውነተኛ የአምላክ ቃል ከሆነ፤ ለእኛ አስፈላጊያችን መሆኑን በዚህ ጥናታችን እንመለከታለን፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን አስፈላጊነት በስፋት ከማየታችን በፊት፣ አስቀድመን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንድነት እንመልከት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይና አዲስ ኪዳን ተብሎ በሁለት ክፍል መከፈሉንም ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ በእግዚአብሔር ደራሲነትና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወደ ዐርባ በሚደርሱ ጸሐፊዎች፣ በተለያየ የጊዜ ርዝመትና በተለያየ ባሕል ውስጥ በኖሩ፣ በተለያየ የዕውቀት ደረጃ በነበራቸውና በተለያየ የጂኦግራፊ አቀማመጥ (ክልል) ውስጥ በሚኖሩ በካህናት፣ በነብያት፣ በነገሥታትና በተራ ሰዎች ተጽፏል፡፡ ቃሉ ለመጻፍ የወሰደው ጊዜ፣ ብሉይ ኪዳን 1400 ዓመት፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ 100 ዓመት ሲሆን፤ በጠቅላላው 1500 ዓመት ያህል እንደ ወሰደ በጥልቀት ያጠኑት ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሁኔታ የተጻፈ ቢሆንም ጸሐፊዎቹ በአስተላለፉት መልእክት፣ ዓላማ፣ ይዘቱና ሀሳቡ በሊቃውንቱ ጥናት መሠረት፣ መጋጨትና መጣረስ በፍጹም አልተገኘበትም፡፡ ምክንያቱም የቃሉ ምንጭና እንዲጻፍ ትዕዛዙን የሰጠው እግዚአብሔር ራሱ በመሆኑ፡፡ (ዘጸ.17፡14፣ ኢያ.24፡26)
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቢመስልም በውስጡ 66 መጻሕፍትን ያካተተ ስብስብ ነው፡፡ ዋና መልእክቱም ክርስቶስ ስለ ሚወለድበት ሕዝብ ታሪክ መተረክ፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣት/መወለድ፣ መከራ መቀበል፣ ከሞት መነሣትና ማረግ፤ እንዲሁም ተመልሶ በመምጣቱ ዙሪያ የተጻፈ፤ ለሰው ልጆች ሕይወት ሰጪ መልእክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ለማዳን ሕግ በመስጠትና በነቢያት የተለያየ መልእክቶች በማስተላለፍ፤ በመጨረሻም በልጁ በኩል ስለ ማዳን ሥራው እንደ ተናገረን ያሳየናል፡፡ (ዕብ. 1፡1-2) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን 39 አዲስ ኪዳን 27 ተብሎ የተለያየ ቢመስልም አንድነት ያለውና አንድነቱን የጠበቀ መጽሐፍ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡
6.2 የቃሉ ሥልጣን
መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን አለው የምንለው ሥልጣን ካለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ መጣ ነው፡፡ ቃሉ በመገለጥና በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ወደ ሰዎች እንደ መጣ፣ ቀደም ባሉት ጥናታችን ተመልክተናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ በቃሉ ሲናገር ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ›› (ማቴ.28፡18) ብሎ በተናገረው መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ካለው ጌታ የመጣ በመሆኑ ሥልጣን እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ ሥልጣንም ስለ አለው በየዘመናቱ ሰውን ስለ ኃጢአቱ በመውቀስና ክርስቶስን በማሳየት ሕይወት ሲለውጥና ከእግዚአብሔር ጋር ሲያገናኝ ኖሮአል፡፡
ሰዎች ሊያጠፉት ወረቀቱን ቢቀዳድዱትም ቢያቃጥሉትምና ባሕር ውስጥ ቢጨምሩትም፤ ተግዳሮትን ሁሉ ተቋቁሞ በተለያየ ቦታ ተቀብሮ ተገኝቶአል፡፡ እንዲሁም ይበልጥ በሰው ልብ ውስጥ የተጻፈውን ቃል በፍጹም ሊያጠፋት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ሐሳብ ላይ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በባሕል ላይ፣ በመሪዎችና በሰባኪዎች፣ በስሜቶቻችንና በተሞክሮዎቻችን ሁሉ ላይ የበላይ ባለ ሥልጣን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያቀደውን የደህንነት (ድነት) ዕቅድ፣ የፈቃዱን መልካም ሐሳብና ዓላማ በሙላት ይዞ በተገለጠ ጽሑፍ የፈቃዱን ምስጢር አስታውቆናል፡፡
በዚህ መሠረት ቃሉ አንድነትና ሥልጣን ያለው በመሆኑ ዛሬም የሰውን ሕይወት ይለውጣል፡፡ ዛሬም ሕይወታችን በዚህ ቃል ተለውጦ ጌታን የምንከተል ወገኖች ሁሉ ይህን የትምህርታችንና የልምምዳችን የበላይ ልናደርገው ይገባናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዘመን በአብርሆተ-መለኮት ለሕይወታችን ሊናገረንና መመሪያ ሊሰጠን ይችላል፤ ነገር ግን አገኘን የምንለው መመሪያ ከቃሉ ጋር የሚጋጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ቃሉ ሚስትህን ውደድ እያለ፣ ፍታ የሚል መገለጥ ከመጣ ከቃሉ ውጭ ስለሆነ ልንቀበለው አይገባም፡፡ ጠላትህን ውደድ እያለ ግደለው የሚል መልእክት ከመጣ መቀበል አይኖርብንም፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች መጽሐፍ ቅዱስ ለሕይወታችን እጅግ አስፈላጊያችን በመሆኑ፤ ራሳችንን ለእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን እናስገዛ፣ ሕይወታችን ይቀደስበታል፣ ያድግበታል፣ ይባረክበታል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል አስፈላጊነት የጣሉ ግለ ሰቦች፣ ኀብረተ ሰቦችና አገሮች ከትልቅ ውድቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ እኛም አሰፈላጊውን የጌታን ቃል እየታዘዝን እንዳንጥለው በጥንቃቄ እንጠብቀው፡፡
0 Comments